ሰዊዘርላንድ 300 ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ወደ አገራቸው ለመመለስ መወሰኗን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ኮነነ
(ኢሳት ዜና መጋቢት 27 ቀን 2010 ዓ/ም) የስዊዘርላንድ መንግስት ጥገኝነት የጠየቁ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ከኢትዮጵያ የደኅንነት ባለስልጣናት ጋር ስምምነት በማድረግ ወደ ትውልድ አገራቸው ለመመለስ ውሳኔ አሳልፏል። ውሳኔውን ተከትሎ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ድርጊቱን በመኮነን መግለጫ አውጥተዋል።
ስደተኞቹ ካለምንም ሕጋዊ የጉዞ ሰነድ ወደ ስዊዘርላንድ የገቡ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ የደህንነት ሰራተኞች ማነታቸውን የመለየቱን ስራ እንዲሰሩ ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ይህን ውሳኔ ተከትሎ በስዊዝርላንድ ዓለምአቀፍ የአምነስት ኢንተርናሽናል ቅርንጫፍ ”ካለምንም ጥርጥር በባለስልጣናት የተወሰደ ፍጹም የሆነ የጫካኔ እርምጃ” ሲል ድርጊቱን አጥብቆ ኮንኖታል።
በአሁኑ ወቅት ቁጥራቸው ከ1 ሽህ 500 በላይ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በስዊዘርላንድ ይኖራሉ። 300 የሚሆኑ ስደተኞች ወደ አገራቸው ይላካሉ ተብሎም ይጠበቃል። ስዊዘርላንድ ውስጥ ኗሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊያንም የስደተኞቹ የአውሮፓ ኅብረትንና የስዊዘርላንድ መንግስትን ውሳኔ ተቃውመውታል።
የስዊዘርላንድ ፍርድ ቤት ቁጥራቸው ከ3 ሽህ 200 በላይ የሚሆኑ ኤርትራዊያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱም ውሳኔ አሳልፏል።