መስከረም ፳፰(ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-“የመከላከያ ሰራዊቱ ያዛዥነት ቦታዎች በአንድ ብሄር ቁጥጥር ስር ነው” በሚል ተደጋጋሚ ትችት የሚደርስበት ኢህአዴግ፣ ሰራዊቱን ህብረብሄራዊ ማድረጉን ገለጸ።
የተለያዩ የመንግስት ሰራተኞች እንዲወያዩበት ተብሎ በኢህአዴግ የተዘጋጀው ሰነድ የትምክት ሃይሎች ” በአገራችን የአንድ ብሄር የበላይነት ያለ ለማስመሰል የማያደርጉት ሙከራ የለም” ካለ በሁዋላ፣ ሰራዊታችን በህገ መንግስቱ መሰረት
የተዋቀረ ህብረብሄራዊ ሰራዊት ሆኖ እያለና በመጀመሪያዎቹ አመታት ከትግሉ ጋር ተያይዞ የነበረውን አለመመጣጠን ረጅም ርቀት ተጉዘን እያለ ይህ እንዳልሆነ ለማስመሰል በትግራይ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ
የማያቋርጥ የማጥላላት ዘመቻ ያካሂዷሉ” ብሎአል። የትምክት ሃይሉ የሚኒስትርነት ሃላፊነትን እየቆጠረ ይህ ብሄር ከዚያኛው የበለጠ የደረሰው በማስመሰል ስርዓቱ የእኩልነት ሳይሆን የመበላለጥና መስሎ እንዲታይ ይጥራል
ሲል ሰነዱ ያመለክታል። ኢህአዴግ የመከላከያ ሰራዊቱ ህብረብሄራዊ ሆኗል ቢልም ግንቦት 7 ከአራት አመት በፊት በመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ የነበረውን የብሄር ተዋጽኦ ያጠናበትን ሰነድ እንደገና ገምግሞ ሰሞኑን ይፋ
ባደረገው ጥናታዊ ጽሁፍ፣ ተቋሙ ጭራሽ ከድጡ ወደማጡ እያዘገመ ነው ብሎአል።
ግንቦት7 በጥናቱ ከ10 ከከፍተኛ ወታደራዊ እዝና ቁጥጥር ዘርፎች የበላይ ሃለፊዎች ከሆኑት 10 ባለስልጣኖች ውስጥ 9ኙ የትግራይ ብሄር ተወላጆች ናቸው።ጄል ሳሞራ፣ ሌ/ጄ ሰአረ መኮንን፣ ሜ/ጄኔራል ኢብራሂም
አብዱጀሊል፣ ብ/ጄ ገብሬ ዲላ፣ ሜ/ጄ ብርሃኔ ነጋሽ፣ ብ/ጄ ክንፈ ዳኘው፣ ሌ/ጄ ዮሃንስ ገ/መስቀልና ብ/ጄ መሃመድ ኢሻ የትግራይ ብሄር ተወላጆች ሲሆኑ፣ ሜ/ጄ አደም መሀመድ ብቻ የአማራ ተወላጅ መሆናቸው
ተጠቅሷል። ከኦሮሞና ከሌሎች ብሄሮች አንድም በከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥነት የተቀመጠ ሰው የለም።
ከአምስቱ የእዝ ሃላፊዎችም 4ቱ የትግራይ ተወላጆች ሲሆኑ፣ አንዱ ከኦሮሞ መሆኑ በጥናቱ ተጠቅሷል። ከምድር ጦር ክፍል ከማእከላዊ እዝ ከ6ቱ አዛዦች 4ቱ የትግራይ ተወላጆች ሲሆኑ፣ አንዱ የአማራ ሌላው የአገው ተወላጅ
መሆናቸው ተመልክቷል። ከሰሜን እዝም እንዲሁ ከ6ቱ ሁለቱ ብቻ የሌላ ብሄር ሲሆኑ ሌሎቹ የትግራይ ተወላጆች ናቸው። ከደቡብ መስራቅ እዝ ሁለት ኦሮሞ፣ ሁለት ትግሬና አንድ አማራ የሚገኙ ሲሆን፣ ከምእራብ እዝ ሁለት
ትግሬ፣ አንድ ኦሮሞና አንድ ድብልቅ እንደሚገኙ በጥናቱ ተጠቅሷል።
በመከላከያ ሚኒስቴር የውጊያ አገልግሎትና ድጋፍ ሰጪ ተቋማት ውስጥ 13 ትግሬዎች፣ አንድ አማራና አንድ ኦሮሞ እንደሚገኙ ጥናቱ አሳይቷል። ወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያ አዛዦች ውስጥ ከ10 ባለስልጣነቱ ውስጥ 7ቱ
የትግራይ ተወላጆች ናቸው። በሌላ ዜና ደግሞ ገዢው ፓርቲ እያንዳንዱ የቀበሌ ሊ/መንበር እስከ 15 ወታደሮችን መልምሎ እንዲያመጣ መተዛዘዙን የደረሰን መረጃ ያመለክታል። መከላከያን ጥለው የሚጠፉ ወታደሮች
መጨመራቸው ለሰራዊት ምልመላ መነሻ መሆኑን ምንጮች አክለው ገልጸዋል። ማንኛውም ከ8ኛ ክፍል በላይ የትምህርት ደረጃ ያለው ሰው እንዲመለመል መመሪያው ያዛል።