በሰሜን ጎንደር ዞን የሚገኙ ወረዳዎች በመሰረተ ልማት በከፍተኛ ደረጃ ወደ ኋላ መቅረታቸውን  የወረዳ አመራሮች  በግልጽ በማቅረባቸው ከክልልና ዞን ባለስልጣናት ግሳጼ እንደደረሰባቸው ተናገሩ፡፡

መስከረም ፳፱(ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በጎንደር ዩኒቨርስቲ አመታዊ የተማሪዎች ምረቃ በዓል ብቅ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስቴር ሐይለማርያም ደሳለኝ ህብረተሰቡ ምን ይለናል የሚለውን ለማዳማጥ ከሰሜን ጎንደር ከተሰባሰቡ የወረዳ አመራሮች ጋር ባደረጉት

ድንገተኛ ስብሰባ የወረዳ አመራሮች በንባብ እንዲያሰሙት ከየዞን ሃላፊዎች የተሰጣቸውን ማስታወሻና አቅጣጫ ወደጎን በመተው መንግስት እንዲያስተካክላቸው በጠየቁዋቸው ጥያቄዎች ምክንያት ከስብሰባው በኋላ ወከባና ማስፈራሪያ እንደደረሰባቸው ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ በተደጋጋሚ ለከፍተኛ አመራሮች በህዝባዊ ስብሰባዎች በየጊዜው ከማቅረብ አልፎ ከዚህ ስብሰባ በፊት በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ይፈታሉ የተባሉት የጸጥታ ፣የመንገድ ፣የኤሌትሪክ ፣የስልክ ፣የመሬት ፣ የመልካም አስተዳደር እና ውሃ ችግሮች ወራቶች

ቢያልፉም አንዱም አለመፈታቱ በህዝቡ እና ወረዳ አመራሮች መካከል ቅሬታ በመፈጠሩ የወረዳ አመራሮች ራሳቸውን ከህዝብ ወቀሳ ነጻ ለማውጣት ጉዳዩን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢቀርብ መፍትሄ ሊያገኝ ይችላል ብሎ ከማሰብ ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ስብሰባ ንግግራቸውን ለዘብ በማድረግ የየአካባቢቸውን ህዝብ ችግር ከተሰጣቸው አጀንዳ ውጭ ቢናገሩም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀረቡትን የህብረተሰብ ችግሮች እንደግብአት እንቆጥራቸዋለን፣ ለወደፊቱ ከዚህ በመነሳት ችግሮቹ የሚወገዱበትን መንገድ ከክልሉ

መንግስት ጋር በመሆን እናስተካክላለን በማለት መልሰው ወደ ክልሉ መንግስት መግፋታቸው ከችግራችሁ ጋር አብራችሁ ኑሩ የማለት ያህል መሆኑ ብዙዎችን አመራሮች ያሳዘነ መሆኑን  ለዘጋቢያችን ተናግረዋል፡፡

ለክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ከአሁን በፊት ቢቀርቡም ምላሽ ያልተሰጠ መሆኑን የገለጹት ቅሬታ አቅራቢ፣  በተለይ ለአመታት በዘለቀው የሱዳን አርሶ አደሮች እና የኢትዮጵያ ደንበር አካባቢ ነዋሪዎችን ግጭት ከመከላከል  አኳያ መወሰድ ያለበትን መፍትሄ በተደጋጋሚ

በህዝባዊ ስብሰባዎች ቢቀርብም ለውጥ ባለመገኘቱ ቅሬታውን በድጋሚ ማቅረባቸውን አመራሮቹ ተናግረዋል፡፡

የሱዳን መከላከያ ሰራዊት  በድምበር አካባቢ የሰፈረ በመሆኑ በሚከሰቱ ግጭቶች ፈጥኖ በመገኘት ለዜጎቹ ከለላ ሲሆን ፤ በኢትዮጵያ በኩል የአካባቢው ሚሊሺያ ብቻ ግጭቶችን ለመመከት የሚያደርገው እንቅስቃሴ አመርቂ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል መንግስት ከ23 ዓመታት በኋላም በተለያዩ የልማት ስራዎች እንደ አጎራባች ክልሎች የህብረተሰቡን ችግር ማዕከል አድርጎ አለመስራቱ፣ በተደራጀ ዕቅድና በጀት አለመመራቱ ተደራራቢ ችግሮች በህብረተሰቡ ላይ እንዲደርስና ህብረተሰቡ እንዲያማርር

ምክንያት ሆኗል ሲሉ ታዛቢዎች ይገልጻሉ፡፡