ሰሜንና ደቡብ ኮሪያ ተፋጠዋል

መጋቢት ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በሰሜን እና በደቡብ ኮሪያ መካከል ላለፉት 60 አመታት ጸንቶ የቆው የተኩስ አቁም ስምምነት መፍረሱን የሰሜን ኮሪያ ባለስልጣናት ገልጸዋል። የሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ ቃል አቀባይ እንደገለጡት በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የተኩስ አቁም ስምምነት ከዛሬ ሰኞ ጀምሮ ተሽሯል።

ሰሜን ኮሪያ የጸጥታው ምክር ቤት ባለፈው ሳምንት የጣለውን ከባድ ማእቀብ በመቃወም  የሚሳኤል እና የኒውክሊየር ሙከራዎችን በማድረግ ላይ ናት። የሰሜን ኮሪያ የሰራተኞች ጋዜጣ ሮዶንግ ሲሙን ይዞት በወጣው ዘገባ እንደገለጠው የጸጥታው ምክር ቤት ያስተላለፈው ማእቀብ ጦርነት እንደማወጅ የሚቆጠር ነው።

ሰሜን ኮሪያ ራሱን እያዘጋጀት ባለችበት ወቅት፣ አሜሪካና ደቡብ ኮሪያም ወታደራዊ ጉድጓዶችን በሁለቱ አገራት ድንበር ላይ እየቆፈሩ መሆናቸው ታውቋል።

በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ፍጥጫ እየተባባሰ መምጣት ፣ ላለፉት 60 አመታት አንጻራዊ ሰላም የነበረውን የኮሪያ ፔንሱዌላ የ አውዳሜ ጦርነት ቀጣና ሊያደርገው ይችላል ተብሎ ተስግቷል።