ሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤቱን እንዲለቅ ትእዛዝና ማስጠንቀቂያ ተሰጠው::‪

፲፬( አስራ አራት )ቀን ፳፻፮ /  ኢሳት ዜና :- ሰማያዊ ፓርቲ ግንፍሌ አከባቢ የሚገኘውን እና በጽ/ቤትነት የሚጠቀምበትን ቢሮ  በአስቸኳይ እንዲለቅ  ትዕዛዝ ደረሰው።

በዛሬው እለት ከሰኣት  በኋላ አቶ ሄኖክ የተባሉ አከራዩ ከአራት ግለሰቦች ጋር በመምጣት ፦”ቤቱን ለነዚህ ግለሰቦች ስለሸጥኩላቸው እንድትለቁላቸው” ሲሉ ከውል ውጪ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።

ቤቱን ገዛሁት የሚለው  ግለሰብ በበኩሉ፦”ቤቱን የኔ  ስለሆነ በአስቸኳይ እንድትለቁልኝ፣ ካልሆነ የራሴን እርምጃ እወስዳለሁ” ሲል አመራሮቹ ላይ ዝቷል::

ይህ ግለሰብ በማይመለከተው ጉዳይ በመግባት፦” ከዚህ በፊትም ልቀቁ ተብላችሁ በተደጋጋሚ እንደተነገራችሁ መረጃው አለኝ፤ በቶሎ የማትለቁ ከሆነ እርምጃ ይወሰድባችሁዋል” በማለት በአመራሮቹ ላይ ቁጣ የተቀላቀለበት ዛቻ በመዛት ሄዷል:;

ሰማያዊ ፓርቲ ከዚህ ቀደም በመነን አከባቢ ተከራይቶት የነበረውን ጽ/ቤት ገና ሳይገባበት በዝግጅት ላይ እንዳለ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎችና እና ቅጥረኞች በተቀናጀ አፈናና ሀይል የተቀላቀለበት እርምጃ ቢሮውን እንዳስለቀቁት ይታወቃል::

ቀደም ሲል ከሰማያዊ ፓርቲ የተነጠቀውን ቢሮ  የወሰደው ካድሬም፤ ፔንሲዎን ከፍቶ እየነገደበት እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።

የፓርቲው ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ካለፉት ሳምንታት ጀምሮ ፓርቲያቸውን በውጪ አገራት ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በማስተዋወቅ ላይ እንደሚገኙ ይታወቃል።