ሰኔ ፪ (ሁለት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ ሚያዚያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም አረመኔው የአይ ኤስ አይ ኤስ ቡድን በዜጎቻችን ላይ የፈፀመውን አሰቃቂ ግድያ ለመቃወም መንግስት በጠራው
ሰልፍ ላይ በራሱ በመንግስት ላይ ተቃውሞ ያሰሙ ዜጎችን በእለቱ በአሰቃቂ ሁኔታ በኃይል ከመደብደብና ከማዋከቡም በተጨማሪ አልፎ ተቃውሞ አነሳስተውብኛል ብሎ ያሰባቸውን በቦታው ያልተገኙ ዜጎችን ጨምሮ ስጋት አድርጎ የሚቆጥራቸውን የሰማያዊ፣ የቀድሞው አንድነትና መኢአድ አባላትን እንዲሁም ሌሎች ወጣቶችን በገፍ አስሯል ብሎአል።
በርካታ ” የሰማያዊ፣ የቀድሞው አንድነትና መኢአድ አባላት እንዲሁም ሌሎች ወጣቶች በሰልፉ ሰበብ ታስረው በካድሬዎችና ደህንነቶች የሐሰት ምስክርነት እየተወነጀሉ እንደሚገኙ የገለጸው ፓርቲው፣ በሌሎች ላይም ተመሳሳይ ክስና የሐሰት
ምስክርነት እየተዘጋጀ ከመሆኑም በላይ ስርዓቱ በለውጥ ፈላጊ ወጣቶች ላይ ተመሳሳይ እርምጃ በመውሰድ ትግሉን ለማዳከም ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው ” ይላል።
የምርጫውን ውጤት ” ተከትሎ ተቃውሞ ሊያስነሱብኝ ይችላሉ ያላቸውን የሰማያዊ፣ የቀድሞው አንድነትና መኢአድ አባላትን ከየክፍለ ሐገሩ አድኖ በማሰር ተቃውሞውን ለማዳፈን እየጣረ ” መሆኑንም ፓርቲው አስታውቋል።
ስርዓቱ የሕዝብን ተቃውሞ ለማዳፈንና የነፃነት ድምፅ የሚያሰሙ ወገኖችን ቅስም ለመስበር የሚያደርገው መሯሯጥ ብዙ በደልና መገፋትን ተሸክሞ የሚኖረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ለበለጠ ትግል እንዲነሳ ያደርገዋል የሚለው ፓርቲው፣
የገዥው ቡድን የጦር ጠማኝ ጀብደኝነትና ፀብ አጫሪነት ሐገራችንን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ቢወስዳት ለሚመጣው ጥፋትና አለመረጋጋት በብቸኝነት ኃላፊነትን የሚወስድ መሆኑን ማወቅ አለበት ሲል አክሏል።
በየእስር ቤቱ የሚማቅቁ አባሎቻቸው እንዲፈቱ በማንአለብኝነት አባሎቻቸውን የሚያሳድዱ ካድሬዎችና ሰላዮች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ፓርቲው ጠይቋል።