ኀዳር ፳፯ (ሃያ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በገዛ አፈሙዙ መቃብሩን የሚቆፍር የሽንፈትን ጽዋ ይጎነጫል በሚል መሪ ቃል የአዲስ አበባ አዲሱ ማስተር ፕላንን በመቃወም ሰላማዊ ተቃውሟቸውን የሚያሰሙ ዜጎች ላይ በኃይልና በጠብመንጃ ለመመለስ የሚደረገውን አግባብነትና ኃላፊነት የጎደለው ጭፍን ተግባር እንደሆነ የሰማያዊ ፓርቲ ብሔራዊ ምክር ቤት ድርጊቱን ኮንኖ የአቋም መግለጫ አውጥቷል።
ኢህአዲግ መራሹ መንግሥት በኢትዮጵያ ምድር ላይ የተከለው የጎሳ ፌዴራሊዝም ችግር ምን ያህል አስከፊ እንደሆነና ውጤቱም የዜጎችን ሞት፣ እስራት፣ ስደት፣ የንብረት ውድመትና የትምህርት መስተጓጎል እያስከተለ እንደሆነ ሰማያዊ ፓርቲ ገልጾ፣ የአዲስ አበባ ዙሪያ ነዋሪዎችም ሆኑ በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚፈልጉት ልማትም ሆነ እድገት በእኔ አውቅልሃለሁ ባዩ የኢህአዲግ አንባገነናዊ ልማትና የጎሳ ፌዴራሊዝም ሳይሆን፣ በሕዝብ ፍላጎትና ስምምነት ላይ የተመሠረተ ልማትና እድገት ብቻ እንደሆነና አንባገነኑ መንግሥት እየተከተለው ያለውን የዜጎችን ጥያቄ በኃይልና በጉልበት ለማፈን ከሚያደርገው ፀረ ዲሞክራሲያዊ ድርጊቱ እንዲቆጠብም አሳስቧል።
የአዲስ አበባ ዙሪያ ማስተር ፕላንን በኃይል ለመተግበር ሲባል ስለሞቱት፣ ስለታፈሱት፣ ስለተሰደዱትና ስለተሰወሩት ዜጎች ጉዳይ የሚያጣራና በጎንደርም ከተማ በሚገኘው እስር ቤት ስለተከሰተው የእሳት ቃጠሎና ከርሱም ጋር ተያይዞም ስለተፈፀመው የጅምላ፡ፍጅት ጉዳይ የሚያጣሩ ገለልተኛ የሆኑ አጣሪና አካል ተቋቁመው ስለተፈጠረው ዘግናኝና ኢሰብአዊ ተግባር መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትክክለኛውን መረጃ እንዲያገኝ እና ወንጀለኞችም ለፍረድ እንዲቀርቡ ጠይቋል።