ጥቅምት ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ የአሁኑ ሰመጉ ኢሳት ከአንድ አመት በፊት የሰራውን፣ በሶማሊ ክልል በየረር ጎሳ አባላት ላይ የደረሰውን እልቂት የተመለከተውን ዘገባ ሰራተኞቹን ወደ ስፍራው ልኮ ያረጋገጠበትን ዘገባ ይፋ አድርጓል።
ኢሳት ጥቃቱ እንደተፈጸመ ወዲያውኑ ዜናውን ይፋ አድርጎ የነበረ ሲሆን ፣ በታህሳስ ወር 2006 ዓም የየረር ባሪ የአገር ሽማግሌዎችን አነጋግሮና ለጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም የተጻፈውን ደብዳቤ ዋቢ አድርጎ ” በሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ ሙሃመድ ኡመር እና ጄኔራል አብርሃም በቅጽል ስማቸው ኳርተር የሚመራው ልዩ ሚሊሺያ ታህሳስ 1 እና 2 በከፈተው ተኩስ በትምህርት ላይ የነበሩ ህጻናትንና ወጣቶችን ጨምሮ 47 ሰዎችን ገድሏል ሲል ይፋ አድርጎ ነበር።
ኢሳት በወቅቱ በሰራው ዘገባ የማቾችን ስም ዝርዝር ይፋ ከማድረግ ባሻገር ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሰመጉ አቤቱታ ለማሳማት የሄዱ የአገር ሽማግሌዎች መታሰራቸውንና ከእነሱም መካከል 2ቱ በእስር ቤት በደረሰባቸው እንግልት መሞታቸውን ዘግቦ ነበር።
ሰመጉ ባወጣው 139ኛ ልዩ መግለጫ የልዩ ሚሊሺያ አባላት 65 ሰዎችን መግደላቸውንና 150 የሚሆኑ የየረር ባሪ እና ዱቢ ጎሳ አባላትን መቁሰላቸውን ይፋ አድርጓል።
የጎሳው አባላት ራሳቸውን ለማስተዳደር እንዲችሉ በመጠየቃቸው መገደላቸውን የዘገበው የሰብአዊ መብት ድርጅቱ፣ የጎሳው አባላት ቤታቸው እንደተቃጠለባቸውና ንብረታቸውም እንደወደመባቸው ይፋ አድርጓል።
በአካባቢው የተዘዋወረው የሰመጉ አጣሪ ቡድን ድርጊቱ በልዩ ሚሊሺያው መፈጸሙን ማረጋገጡን ጠቅሷል። ከሟቾች መካከል 4 አመቱ አህመድ አብዲ አሊ፣ የ5 አመት እድሜ ያለው አሊ ኡስማን አብደሌ፣ የ8 አመት እድሜ ያለው ኑር አብዱሰመድ ይገኙበታል። ኢሳት በወቅቱ ባካፍ ድል እየተባለ በሚጠራው ትምህርት ቤት ተኩስ ተከፍቶ ህጻናት ማለቃቸውንም ገልጾ ነበር።
ይህ አሰቃቂ ድርጊት የተፈጸመው ክልሉ የብሄር ብሄረሰቦችን በአል ለማክበር ሽርጉድ ይል በነበረበት ወቅት ነው። የጎሳው አባላት ባህላቸውና ቋንቋቸው እንዲከብራለቸው በተደጋጋሚ መጠየቃቸው ለግድያ ዳርጓቸዋል። በቃለፎ ፣ ሙስታሂልና ፈርፌር ወረዳዎች ውስጥ ከ 300 ሺ የማያንሱ የሬርባሪ ጎሳ አባላት ይኖራሉ።
ልዩ ሚሊሺያውን ወደ አካባቢ በመላክ በህዝብ ላይ እልቂት የፈጸሙት የክልሉ ፕሬዚዳንት እንዲሁም ክልሉን ከበላይ ሆነው የሚመሩት ጄኔራል አብርሃ እስካሁን ለፍርድ አልቀረቡም። አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝም ለቀረበላቸው አቤቱታ መልስ አልሰጡም።
ሰመጉ በማጠቃለያው የአገሪቱ የሰብአዊ መብት ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ብሎአል። ህገወጥ ግድያ፣ አካል የማጉደል፣ ንብረት የማውደምና ቤት የማቃጠል ወንጀል የፈጸሙ የጸጥታ ሃይሎች ህግ ፊት እንዲቀርቡና ወንጀሉ እንዲፈጸም ትእዛዝ ሰጡ ባላስልጣናትም በህግ እንዲጠየቁ አሳስቧል።