ሰመጉ በሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞን ከህዳር 24 እስከ የካቲት 4 ቀን 2010 ዓ.ም 17 ሰላማዊ ዜጎች በፀጥታ ሃይሎች በግፍ መገደላቸውን አስታወቀ
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 04 ቀን 2010 ዓ/ም ) በአማራ ክልል በሰሜን እና ደቡብ ወሎ ዞን በሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈፀመውን ኢሰብዓዊ የመብት ጥሰቶች አስመልክቶ ሰመጉ በ145ኛው ልዩ መግለጫው፣ ከህዳር 24 እስከ የካቲት 4 ቀን 2010 ዓ.ም በሰሜን ወሎ ወልዲያ ከተማ፣ ወልዲያ ዙሪያ ወረዳ፣ ሮቢት፣ ቆቦ፣ መርሳ፣ ኡጌጋሳ፣ በደቡብ ወሎ ደሴ ከተማ ሰለሙያዎችን ልኮ የማጣራት ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጿል።
በአካባቢው የተፈፀመውን ዘግናኝ ጭፍጨፋ ለማጣራትም በቀጥታ ከተጎጂዎችና ከተጎጂ ቤተሰቦች አቤቱታና ማስረጃ ተቀብሏል። ከምስክሮች የምስክርነት ቃል፣ ድርጊቱ በተፈፀመባቸው አካባቢዎች በአካል በመገኘት ሁኔታውን በዓይን በማየትና በማጥናት፣ ከአካባቢው ነዋሪዎችም በመረዳት፣ በተጨማሪም የሠነድ፣ የፎቶግራፍና የቪዲዮ ማስረጃዎችን በመቀበል እና በመመርመር መረጃ ለመሰብሰብ መቻሉን ሰመጉ አስታውቋል።
በሰሜን ወሎ ዞን ብቻ 17 ሰላማዊ ዜጎች በፀጥታ ሃይሎች በግፍ መገደላቸውን የምርመራ ቡድኑ በምስል አስደግፎ አውጥቷል። ከሟቾቹ መሃከልም ታዳጊ ህጻናትና አዛውንቶች ይገኙበታል። ከሟቾቹ በተጨማሪም በ20 ሰላማዊ ዜጎች ላይ ከባድና ቀላል አካላዊ ጉዳቶች ደርሶባቸዋል። በተጨማሪም በ5 የፀጥታ አስከባሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱንም የምርመራ ቡድኑ ገልጽዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤትን፤ የሰሜን ወሎ ዞን ፖሊስ መምሪያ ማንኛውንም አይነት ማስረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆኑም። በዚህም ምክንያት ሰመጉ መርማሪዎቹ ተንቀሳቅሰው ያሰባሰቡትን ማስረጃዎችን ብቻ ለማቅረብ መገደዱን ገልጿል።
መንግስትህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በቂ ትኩረት በመስጠትና በማዳመጥ፣ ለግጭቶቹ መቀስቀስ ምክንያት የሆኑትን ምንጮች በማጥናት፣ ህጋዊና ዴሞክራሲያዊ እርምጃዎችንበመውሰድ በሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ እጃቸው ያለበት አካላትን ተጠያቂ በማድረግ፣ዜጎችን በሀገራቸው በእኩልነትና በሰላም የሚኖሩበትን ሁኔታ በአስቸኳይ እንዲያመቻቹ ይገልባ ሲል ሰመጉ ሪፖርቱን አጠቃሏል።