ህዳር ፲፫ (አስራ ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ(ሰመጉ) ወይም በቀድሞው አጠራሩ ኢሰመጉ “ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የሚወሰድ ከመሬት የማፈናቀል እርምጃ የዜግነት መብቶችን
ማሳጣት የለበትም” በሚል ርዕስ 122ኛውን ልዩ መግለጫ ዛሬ አወጣ፡፡
ሰመጉ በዚህ መግለጫው በለገጣፎ ለገዳዲ ከተማ ስላለው መልካም አስተዳደር ችግሮች፣የመብት ጥሰቶችና የሕዝብ ቅሬታ፣የታሰሩ ሰዎች ዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡
ከአዲስ አበባ ከተማ በሰሜን ምስራቅ በኩል 21 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የለገጣፎ/ለገዳዲ ከተማ በኦሮሚያ
ክልል በፊንፊኔ ልዩ ዞን ሥር በከተማ አስተዳደርነት እንድትመሰረት ተደርጓል፡፡
በአሁን ሰዓት ከተማዋ 2ሺ431 ሄክታር የመሬት ስፋት ያላት ሲሆን የተዋቀረችውም በሁለት ቀበሌዎች ነው፡፡የከተማው ማዘጋጃ ቤት ባሳተመው ወረቀት የህዝብ ብዛቷ ከ 18 ሺ እንደሚበልጥ ቢገልጽም የከተማው አስተዳደር ከንቲባ ቁጥሩ ከአምስት ሺ እንደማይበልጥ መናገራቸውን ሰመጉ በመግለጫው ጠቅሷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ከሕዝቡ ቁጥር በላቀ መልኩ ወደሃያ ሺ የሚጠጋ ካርታ በከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ከሌላ አካባቢ ለመጡ ሰዎች መሰጠቱ የአካባቢው ነዋሪዎች በቅሬታ መልክ ያነሳሉ ብሏል፡፡ ሰመጉ በዚሁ መግለጫው የለገጣፎ/ለገዳዲ ነዋሪ አብዛኛው ህዝብ በግብርና ይተዳደር እንደነበር በማስታወስ አካባቢው ወደከተማነት በመቀየሩ ምክንያት ገበሬው መሬቱን ሲያጣ ሌላ የገቢ ምንጭ ያልተፈጠረለት መሆኑ የመጀመሪያው ችግር መሆኑን ጠቅሷል፡፡
ገበሬዎች ለኢንቨስትመንትና ለመኖሪያ ቤቶች ሲፈናቀሉ ሕግ በሚፈቅደው መሰረት የገበሬው ጥቅም አልተጠበቀም ብሏል፡፡
ገበሬዎችን ከይዞታቸው የማፈናቀሉ ሥራ የተጀመረው በ1998 ዓ.ም መሆኑን ሰመጉ አስታውሶ በወቅቱ በአስተዳደሩና
በህዝቡ መካከል የነበረው ስምምነት፤ ካሳ እንደተጠበቀ ሆኖ ለቤተሰብ አባወራዎች 500 ካሬሜትር፣ዕድሜያቸው ከ18
በላይ ለሆናቸው ወጣቶች 140 ካሬሜትር ቦታ በምሪት ያገኛሉ የሚል ነበር፡፡ ይህ ዕቅድ ገበሬውን ጨርሶ ከሃገሩ
ያለመነቀል ዋስትናን የሚሰጥና በህገመንግስቱ አንቀጽ 40(4) የተመለከተውን መብት በተወሰነ መልኩ ተግባራዊ
የሚያደርግ ነው፡፡ ይህ ባለመተግበሩ ግን ነዋሪው በከፍተኛ ችግርና ቀውስ ውስጥ እንዲወድቅ እንዳደረገው ሰመጉ
በመግለጫው አመልክቷል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች ይህንና መሰል ችግሮች ለመቅረፍ በመደራጀት ችግሩ አገራዊ መፍትሔ እንዲሰጠው በተወሰኑ
ወጣቶች አማካይነት ጥረት መጀመራቸውን መግለጫው ጠቅሶ ሆኖም ሕዝቡ የሚያደርገውን ትግል ለማኮላሸት መስከረም 25
ቀን 2005 ዓ.ም ሰባት ግለሰቦች ማለትም አቶ እንዳልካቸው መንግስቱ፣አቶ ምትኩ ንጉሴ፣አቶ ድርባ ጉዳ፣አቶ
ጌታቸው ተረፈ፣አቶ ሲሳይ ለማ፣አቶ ገመቹ ወርቁ፣አቶ መኮንን ተስፋዬ የአካባቢውን ሕዝብ ለአመጽ አነሳስታቹሃል
በሚል ተይዘው መታሰራቸውን ይፋ አድርጓል፡፡
እነዚህ ወጣቶች ህዝቡ በሰላማዊ መንገድ ችግሩን እንዲገልጽ ባደረጉት አስተዋጽኦ ብቻ ለእስር በመዳረጋቸው የአካባቢው ማህበረሰብ “ያለወንጀል የታሰሩት ወጣቶች ይለቀቁ” በማለት በህብረት በአስተዳደሩ ቢሮ አካባቢ ሰልፍ በመውጣት ተቃውሞውን አሰምቷል፡፡ወጣቶቹ ከአንድ ቀን እስር በኃላ በዋስ የተለቀቁ ሲሆን ይህ ሪፖርት እስከወጣበት ጊዜ ድረስ የተመሰረተባቸው ክስ እንደሌለ ሰመጉ አረጋግጧል፡፡
ሰመጉ በዚሁ ሪፖርቱ የነዋሪዎቹ ጥያቄ የክልሉ መንግስት በአግባቡ እንዲመልስ፣ከመሬት ጋር ተያይዞ የተፈጸሙ
ወንጀሎች እንዲጣሩና የህግ ተጠያቂነት እንዲሰፍን፣ግልጽነት ባልሰፈነበት ሁኔታ የተሰጡ ካርታዎች ለህዝብ ይፋ
እንዲደረጉ፣የኑሮ ዘይቤው ተቀይሮ ገበሬነቱን ያጣው ሕዝብ የኑሮ ዋስትና እንዲረጋገጥ አሳስቧል፡፡
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide