(ኢሳት ዜና–ሕዳር19/2010)በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ/ሕወሃት/ንብረት በሆነው ሰላም ባስ ገራዥ ላት ጥቃት በመፈጸም የተጠረጠሩ ግለሰቦች ክስ ተመሰረተባቸው።
አቃቢ ህግ ግለሰቦቹ ድርጊቱን የፈጸሙት በአርበኞች ግንቦት ሰባት ትዕዛዝ ነው ሲልም አመልክቷል።
አርብ ሕዳር 15/2010 በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች አንተነህ ፋንታሁን፣ኤርሚያስ አለባቸው፣አንድነት ፋንታሁን፣ፍስሃ እያዩና ብርሃኑ ሞገስ የተባሉ መሆናቸውም በክሱ ተመልክቷል።
እኒዚህ በክሱ ላይ የተዘረዘሩት 5 ግለሰቦች ሐምሌ 13/2009 ከሌሊቱ 6 ሰአት ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ልዩ ስሙ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን አካባቢ በሚገኘው የሰላም ባስ ገራዥ ላይ ሁለት የእጅ ቦምብ በመወርወር ጉዳት ማድረሳቸውን አቃቢ ህግ በክሱ ዘርዝሯል።
ግለሰቦቹ ከዚህም በተጨማሪ በመስከረም ወር በኖክ ነዳጅ ማደያ ላይ የአምቦ ውሃ ጠርሙስ በጋዝ በመሙላት መወርወራቸውንም አመልክቷል።
ግለሰቦቹ ጥቃታቸውን በመቀጠል በመንግስት ተሽከርካሪዎች፣በፖሊስ ጣቢያዎችና በሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ላይ ጥቃት ለማድረስ ሲንቀሳቀሱ ደብረብርሃን ከተማ ላይ መያዛቸውን በችሎቱ የተነበበው ክስ ይዘረዝራል።
ግለሰቦቹ ድርጊቱን ለመፈጸም የተንቀሳቀሱት በአርበኞች ግንቦት 7 ትዕዛዝ እንደሆነ በመጥቀስም የሽብርተኝነት ክስ እንደተመሰረተባቸው በክሱ ተመልክቷል።
ኢሳት ሐምሌ 14/2009 ባቀረበው ዘገባ በአዲስ አበባ ከተማ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን አካባቢ በሚገኘው የሰላም ባስ ጋራዥ ላይ ጥቃት መፈጸሙን መዘገቡ ይታወሳል።
አቃቢ ህግ የኢሳትን ዘገባ በማረጋገጥ በግለሰቦቹ ላይ ክስ የመሰረተ ቢሆንም በጉዳዩ ላይ ተጠርጥረው የተያዙት ግለሰቦች ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት ያላቸው ይሁን አይሁን ማወቅ ግን አልተቻለም።
ስልጣን ላይ ያለው መንግስት የሆነ ድርጊት ሲፈጸም በሌላ ጉዳይ የታሰሩ ሰዎችን ከማያውቁት ጉዳይ ጋር አያይዞ እንደሚከስ ሲገለጽ ቆይቷል።
ይህንንም ስልጣን ላይ ያለው ቡድን የትኛውም ወንጀለኛ አያመልጠኝም የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ እንደሚጠቀምበትና ለመጉዳት ያሰባቸውን እንደሚቀጣበትም ሪፖርቶች ያመለክታሉ።