(ኢሳት ዲሲ–ጥር 22/2010)
የኬንያው ተቃዋሚ ፓርቲ መሪና ዕጩ ፕሬዝዳንት የነበሩት ራይላ ኦዲንጋ ራሳቸውን በፕሬዝዳንትነት ሰይመው ቃለ መሃላ ፈጸሙ።
በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው በተገኙበት ቃለ መሃላውን ሲፈጽሙ ለማሰራጨት የተዘጋጁት የሀገሪቱ ሶስት የግል ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በጸጥታ ሃይሎች ተዘግተዋል።
ይህን ተከትሎም በዋና ከተማዋ ናይሮቢ ውጥረት መስፈኑን አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የ72 አመቱ የኬንያ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ራይላ ኦዲንጋ ዛሬ በናይሮቢ ኡሁሩ ፓርክ ቃለ መሃላ በመፈጸም ራሳቸውን የኬንያ ፕሬዝዳት አድርገው ሾመዋል።
ይህንን የቃለ መሃላ ስነ ስርአት ለመዘገብ ተዘጋጅተው የነበሩ ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በዋዜማው ሰኞ በጸጥታ ሃይሎች ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው በኋላ ዛሬ ስርጭታቸውን እንዲያቋርጡ ተደርገዋል።
ሲትዝን፣ኤን ቲቪና ኬ ቲ ኤን ቲቪ የተባሉት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በጸጥታ ሃይሎች ርምጃ ሙሉ በሙሉ የቴሌቪዥን ስርጭታቸው ቢታገድም የራይላ ኦዲንጋን የቃለ መሃላ ስነስርአት በኢንተርኔት አማካኝነት በዩ ቲዩብና በፌስ ቡክ አሰራጭተዋል።
በኬንያ ውጥረት ሰፍኖ የዋለ ሲሆን አንዳንድ ትምህርት ቤቶችም ተዘግተዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በነሀሴ 2017 በኬንያ በተካሄደው ምርጫ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ማሸነፋቸው በሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ቢገለጽም ተፈጸመ በተባለ ግድፈት በፍርድ ቤት ውሳኔ ምርጫው በህዳር በድጋሚ እንዲካሄድ ተደርጓል።
በህዳሩ ምርጫ የተለያዩ ምክንያቶችን በመስጠት ራይላ ኦዲንጋ ባይሳተፉም አሁሩ ኬንያታ ምርጫውን አሸንፈው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱም አጽድቆላቸው ቃለ መሃላ ፈጽመው ለሁለተኛ ዙር ኬንያን መምራት ጀምረዋል።
የኬንያ መስራች አባት የጆሞ ኬንያታ ልጅ የሆኑት ኡሁሩ ኬንያታ የፕሬዝዳንትነቱን መንበር ይዘው ለተጨማሪ 5 አመታት ሀገሪቱን እየመሩ ባሉበት በአሁኑ ሰአት ራይላ ኦዲንጋ ራሳቸውን በፕሬዝዳንትነት ሰይመው ቃለ ማሃላ መፈጸማቸው በሀገሪቱ ውጥረትን አስከትሏል።
በኬንያ ባልተለመደ ሁኔታ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለመዘጋታቸውም ምክንያት ሆኗል።
በኬንያ ፖለቲካ ውስጥ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1992 ጀምሮ መጉላት የጀመሩት ራይላ ኦዲንጋ በተለያዩ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ውስጥ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2001 ጀምሮ አገልግለዋል።
እጅግ አወዛጋቢ በነበረውና ብዙ ደም ባፋሰሰው የ2007 ምርጫም እጩ ፕሬዝዳንት ሆነው ተወዳድረዋል።
ከቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ሞዋይ ኪባኪ ጋር በነበራቸው ፉክክር የተነሳውን ውዝግብና ቀውስ ለመፍታት በስምምነት የስልጣን ማጋራት ስምምነት ተካሂዷል።
በዚህም የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታ በማግኘት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከሚያዚያ 2008 እስከ 2013 ለ5 አመታት የኬንያ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል።
አሁንም እየፈጠሩት ባለው ውዝግብ በድርድር ስልጣን ለማግኘት እየፈለጉ ነው በሚል ትችት እየቀረበባቸው ይገኛል።