ታህሳስ 04 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የፈጠራ የሽብርተኝነት ክስ ከተመሰረተባቸው 24 ተከሳሾች መካከል አቶ አንዷለም አራጌን ጨምሮ 8 ተከሳሾች ለታህሳስ 16 ቀን 2004 ዓ.ም ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ቀጠሮ የተሰጣቸው ቢሆንም፤ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ለታህሳስ 5 ቀን ከፍተኛ ፍርድ ቤት 3 ኛ ወንጀል ችሎት እንዲቀርቡ ትዕዛዝ እንደደረሳቸው የኢሳት ምንጮች አረጋግጠዋል። ፍርድ ቤቱ ባለፈው ቀጠሮ የተከሳሾቹን የ እምነት ክህደት ቃል ከሰማ በሁዋላ የሰዎች ምስክር ለመስማት ለታህሳስ 16 ቀን ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል።
ይሁንና ለጊዜው በውል ባልታወቀ ሁኔታ ቀጠሮው ተሰብሮ ተከሳሾቹ የፊታችን ሀሙስ ታህሳስ 6 ቀን ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ለጠበቆቻቸውና ለማረሚያ ቤቱ ትዕዛዝ መድረሱ ታውቋል።
በነ አቶ አንዷለም አራጌ መዝገብ ከተከሰሱት 24 ተከሳሾች መካከል 8ቱ ማለትም አቶ አንዷለም አራጌ፣ አቶ ናትናኤል መኮንን፣አቶ ዮሐንስ ተረፈ፣አቶ የሸዋስ ይሁንዓለም፣አቶ ክንፈ-ሚካኤል ደበበ፣አቶ ምትኩ ዳምጤ፣ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና አቶ አንዷለም አያሌው ባለፈው ህዳር 20 ቀን በነበራቸው ቀጠሮ ለፍርድ ቤቱ በሰጡት የ እምነት ክህደት ቃል፤የ አቶ መለስ ዐቃቤ ህግ የደረሰውን የክስ ድራማና ቅንብር እንዳልፈጸሙ ማናገራቸው ይታወሳል።