ነሃሴ ፳፪(ሃያ ሁለት)ቀን ፳፻፭ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የበሽር አላሳድ መንግስት በሲቪሎች ላይ የኬሚካል የጦር መሳሪያ ተጠቅሟል በሚል ሰበብ ምእራባዊያን ሀይል እርምጃ ለመውሰድ እየተዘጋጁ ነው።
እንግሊዝ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት አንድ ህግ ረቂቅ ያዘጋጀች ሲሆን ረቂቁም አገሮች በሶሪያ ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ መብት ይሰጣል።
የአየር ላይ ጥቃታቸውን ለመሰንዘር እየተዘጋጁ ያሉት አሜሪካ፣ ፈረንሳይና እንግሊዝ ከቻይናና ከሩሲያ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።
የአላሳድ መንግስት የኬሚካል የጦር መሳሪያ አለመጠቀሙንና ምእራባዊያን አገሪቱን ለመምታት የተጠቀሙበት ስልት ነው ብሎአል።
ኢራን በበኩሏ አካባቢው ወደ አልተፈለገ የጦርነት ቀጣና ያመራል ስትል አስጠንቅቃለች።
እስራኤልም ተጠባባቂ ጦሯን መጥራቷ ታውቋል።
በሶሪያ ግጭት ከተነሳበት ካለፉት 2 አመታት ጀምሮ ከ100 ሺ ያላነሰ ህዝብ አልቋል።