ግንቦት ፲፯ ( አሥራ ሰባት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የኢሳት የአካባቢው ወኪላችን እንደገለጸው በሶማሊ ክልል ለተፈጸመው ከፍተኛ እልቂት ተጠያቂ የሆነውና ከሶማሊ ክልል ፕሬዚዳንት ጋር ከፍተኛ የሙስና ትስስር እንዳለው የሚነገርለት ጄ/ል አብረሃ ወይም በቅጽል ስሙ ኳርተር፣ በሌላው በሙስና በተዘፈቀው ጄኔራል ማሹ በየነ መተካቱ ታውቋል። ጄ/ል አብርሃ ከምስራቅ እዝ ሃላፊነት ተነስቶ የመከላከያ የዘመቻ መምሪያ ሃላፊ ሆኖ ተሹሟል።
ጄ/ል ሳሞራ የምስራቅ እዝ ሃላፊነቱን ሲለቅ ስልጣኑን የተረከበው ጄ/ል አብርሃ፣ እዙን ለረጅም ጊዜ በመምራት ይታወቃል። በአዲስ አበባ ዘመናዊ ህንጻዎችን እና የንግድ ድርጅቶችን መገንባቱን ኢሳት የፎቶ ግራፍ ማስረጃዎችን አያይዞ መዘገቡ ይታወቃል።
እርሱን የተካው ሜጀር ጄ/ል ማሾ ቀደም ብሎ የጅጅጋ ክፍለ ጦር ወታዳራዊ ኮሚሳር ሆኖ በሰራበት ወቅት፣ ሃጎስ የተባለውን ወንድሙን ከምንም አንስቶ ሚሊየነር በማድረግ፣ በኢትዮጵያ አሉ ከሚባሉት ባለሀብቶች ተርታ እንዲመደብ ማድረጉንምንጮች ገልጸዋል።
በ1987 ዓም አቶ ሃጎስ ወደ ጅጅጋ ሲሄድ በከፍተኛ ድህነት ውስጥ እንደነበርና ወንድሙ ኮሎኔል ማሾ የኪስ ገንዘብ ይሰጡት እንደነበር ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ ምንጮች ገልጸው፣ ይሁን እንጅ በአካባቢው ባለው የኮንትሮባንድ ንግድ ልዩ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በወንድሙ በኩል የተከፈተለትን የንግድ መስመር በመጠቀም በ8 ወራት ውስጥ ሚሊየነር ለመሆን መቻሉንና በዚያው አመት ከ11 ዋና ዋና የኢትዮጵያ ባለሃብቶች ጋር ተመርጦ ወደ ጣሊያን ለንግድ ጉብኝት መሄዱን ተናግረዋል።
ጄኔራሉ በአዲስ አበባ በተለያዩ ቦታዎች በወንድሙ ስም ከፍተኛ የንግድ ቦታዎችን ተቆጣጥሮ መያዙንም እነዚሁ ምንጮች ተናግረዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የኦሮሞና የአማራ ወታደራዊ አዛዦች ወደ ተለያዩ አካባቢዎች እንዲቀየሩ መደረጉ ታውቋል። ይህ ነው የሚባል ወታደራዊ ስልጣን የሌላቸው የአማራ እና የኦሮሞ ብሄር ተወላጅ ወታደራዊ ባለስልጣናት ከተወለዱበት ክልል ውጭ እንዲወጡ እና በሌሎች ራቅ ባሉ አካባቢዎች እንዲመደቡ እየተደረገ ሲሆን፣ ይህም የሚደረግበት ምክንያት፣ አመለካከታቸውን በመገምገም የማጣራት ስራ ለመስራት መሆኑን ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
በሌላ በኩል አሁን ካሉት ወታደራዊ እዞች በተጨማሪ ሁለት ተጨማሪ ወታደራዊ እዞችን ለማቋቋም እንቅስቃሴ ተጀምሯል። አማራ ክልል ከሰሜን እዝ በተጨማሪ ቡሬ ከተማ ላይ በሚመሰረት አንድ ተጨማሪ ወታደራዊ እዝ እንደሚመራ ታውቋል።