መስከረም ፳፰(ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-‹ሕግና ሥርዓት የማይቆጣጠረው ማኅበር ጽንፈኛና አሸባሪ የመሆን ዕድሉ የሰፋ ነው››ሲሉ የኢትዮፐያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ተናሩ።
ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ይህን ያሉት ፡ ‹‹የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደራዊ አስተሳሰብ ማበልፀግ›› በሚል መሪ ቃል ከመስከረም 27 እስከ መስከረም 28 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት መስብሰቢያ አዳራሽ
የተጀመረውን ጉባዔ በከፈቱበት ወቅት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግልጽ የሆነ መዋቅር ያላት ቢሆንም፤ በቤተ ክርስቲያን ስም የሚደራጁ ማኅበራት፣ ከመዋቅራዊ ቁጥጥር ውጭ በመንቀሳቀስ ሀብትና ንብረት ያከማቹና እያከማቹ
መሆናቸውን የተናገሩት ፓትርያርኩ፣ ሕግና ሥርዓት የማይቆጣጠራቸው ከሆነ አሸባሪ የመሆን ዕድላቸው የሰፋ ነው ማለታቸውን ሪፖርተር ዘግቧል።
ፓትርያርኩ በዚሁ ንግግራቸው በቤተ ክርስቲያን ስም ለሚንቀሳቀሱ ማኅበራት ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የቤተክርስቲያኗ ልጆች ከቤተ ክርስቲያን መዋቅራዊ ቁጥጥር ውጭ የሚንቀሳቀ ሀብትና ንብረት ማካበት የተከለከለና
በከባድ ወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ይህ ድርጊት እየተስፋፋ ነው፡ያሉት ፓትርያርኩ፣ እየታየ ያለው የማኅበራት ዝንባሌ ሀብት ማካበት፣ ለቤተ ክርስቲያን ብቻ የተፈቀደውን ‹‹አሥራት በኩራት››
ለራሳቸው መሰብሰብ፣ ከቤተ ክርስቲያን ዕውቅና ውጪ የአገር ውስጥና የውጭ ሥራዎችን በሌላቸው ሥልጣን መሥራት- መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ፓትርያርኩ አክለውም፦” ማኅበራቱ በሰበሰቡት ሕገወጥ ሀብት አባቶችን ይከፋፍላሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችን ያሾማሉ፣ ያሽራሉ፡፡ የእነሱን ፍላጎት የማይፈጽሙትን ያስፈራራሉ፣ አካሄዳቸው ለቤተ ክርስቲያኗ ጥንካሬና
ህልውና ፍጹም አደጋ ሆኗል”ብለዋል። ፓትርያርኩ በዚሁ ንግግራቸው -በአድባራትና ገዳማት የመልካም አስተዳደር እጦት መንገሡንና ባለፉት አሥርት ዓመታት የምዕመናን ቁጥር መቀነሱንም አመልክተዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ስለማኅበራት በጎ ያልሆነ አሠራርንሲናገሩ ‹‹ማኅበራት›› እያሉ በወል ስም ከመጥራት ባለፈ የማህበራት ስም ባይጠቅሱም፣ በስብሰባው ላይ የነበሩ ከገዳማትና ከአድባራት የተወከሉ
አስተዳዳሪዎችና ጸሐፊዎች ግን ያስገነባውን ሕንፃ ጭምር እየገለጹ ማኅበረ ቅዱሳን መሆኑን በመጥቀስ በማህበሩ ላይ ዕርምጃ እንዲወሰድ መጠይቃቸውን የጋዜጣው ዘገባ አመልክቷል።
የቤተ ክርስቲያኗ ማንኛውም ገቢ እንደ ገንዘብ ሚኒስቴር በአንድ ቋት ሆኖ በቅዱስ ሲኖዶስ ኃላፊነት እንዲመራ ያሣሰቡት አንዳንድ የጉባዔው ተሳታፊዎች፤ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ይቅርታ ጠይቀው ወደ ቀድሞ ቤታቸው
ይመለሱ ሲሉ ተናግረዋል።