ማህበረ ቅዱሳን ለሚካሄድበት የስም ማጥፋት ዘመቻ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንዲሰጥበት ጠየቀ

ጥቅምት ፭(አምት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ሰንደቅ እንደዘገበው ማህበሩ ጥቅምት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. በአድራሻ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በግልባጭ ደግሞ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት፣ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ለኾኑት ለሁሉም

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ባሰራጨው ደብዳቤ  ማህበሩ” በማያውቀው፣ ጥፋትም ካለ ተጠርቶ ባልተጠየቀበትና መልስ ባልሰጠበት ኹኔታ ፓትርያርኩ ባሉባቸውና በተለያዩ ጊዜያት በተጠሩ ስብሰባዎች የተፈጸምበት የስም ማጥፋት ዘመቻ መደጋገም ደብዳቤውን ለመጻፍ ” አስገድዶታል።

ማኅበሩ ” በየስብሰባዎቹ የሕዝብ መገናኛ አውታሮች እየተጠሩ በማኅበሩ አገልግሎት ምክንያት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የኾኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በስም እየተጠቀሱ ተራ የስድብ ናዳ እንደሚወርድባቸው ” ገልጾ፣ የስም ማጥፋት ዘመቻው ማህበሩንም ሆነ እውነተኛ የቤተ ክርስቲያን አባቶችንና

ምእመናንን በእጅጉ አሳዝኖናል፤›› ብሏል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሕጋዊ ድረ ገጽ ላይ በኢንተርኔት የተለቀቀው ቪዲዮ፣  የቤተ ክርስቲያን አካላት ነን ከሚሉ ሰዎች የማይጠበቅና ‹‹ቤተ ክርስቲያንን ለጠላት መሳለቂያ ለማድረግ››በጥፋት መልእክተኞች የተቀናበረ ነው ማለቱን

ጋዜጣው ዘግቧል።

ቀደም ሲል ከፓትርያርኩ ጋራ የውይይት መርሐ ግብር እንዲያዝለት በተደጋጋሚ ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት ባላገኘበት ኹኔታ ፓትሪያሪኩ የማህበሩን አመራሮች አንድም ቀን ጠርተው ሳያነገሩ   በሌላቸውና ከእውነትነት በራቁ የሐሰት ክሦች ‹‹የስም ማጥፋት ዘመቻ›› እንዲከፈትበት

በመድረጋቸው ቅር መሰኘቱንም አክሎ ገልጿል።

‹‹በቤተክርስቲያን ልጅነታችን በፈቃዳችን ገንዘባችንን፣ ጉልበታችንንና ጊዜአችንን አስተባብረን በምናደርገው ነፃና የፈቃድ አገልግሎት መብታችንን የሚፃረር” ድርጊት ተፈጽሟል ያለው ማህበሩ፣  ኹኔታው በተመሳሳይ መልኩ ከቀጠለ ቤተ ክርስቲያንን እርስ በርሷ የማትናበብ፣ ማእከላዊ አሠራር

የሌላት የሚያስመስልና ለአገልግሎቷ ዕንቅፋት የሚፈጥር በመኾኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉዳዪን በጥንቃቄ መርምሮና አጣርቶ አስቸኳይ ውሳኔ እንዲሰጥበት እንጠይቃለን ብሎአል።

በፓትሪያርኩ በቅርቡ በጠሩት ስብሰባ ላይ ማህበረ ቅዱሳንን በተለያዩ ወንጀሎች የሚከሱ ሰዎች ንግግር ማድረጋቸው የኢትዮፕያውያን የመወያያ ርእስ ሆኖ ሰንብቷል።