ሚድሮክ፤ የመንገድ ፕሮጀክቶቹን እንዲነጠቅ ተወሰነ

ሰኔ ፬ (አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በአዲስ አበባ የመንገድ ጨረታ ዳግም እንዳይሳተፍ ተባለ።

የሼህ መሀመድ ሁሴን  አል-አሙዲ ንብረት የሆነው ሚድሮክ ኮንስትራክሽን  በአዲስ አበባ  የሚገነባቸውን ሦስት የመንገድ ፕሮጀክቶች እንዲነጠቅ ውሳኔ መተላለፉን ሪፖርተር ዘገበ።

ጋዜጣው  የ አዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣንን በመጥቀስ  እንደዘገበው፤ ሚድሮክ  የጀመራቸውን የመንገድ ፕሮጀክቶች  እንዲነጠቅ  የተወሰነው  በተገቢው ጊዜ  አጠናቅቆ ሊያስረክብ ባለመቻሉ ነው።

ከዚህም ባሻገር ሚድሮክ በከተማው የመንገድ ግንባታ ጨረታ ዳግም  እንዳይሳተፍ  ውሳኔ መተላለፉም ተገልጿል።

የባለሥልጣኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ፍቃዱ ኃይሌ እንዳሉት፣ ሚድሮክ ከአዲስ አበባ አስተዳደርም ሆነ ከባለሥልጣን መሥርያ ቤቱ ፕሮጀክቶቹን እንዲያጠናቅቅ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎች ቢሰጡትም፤ ሥራውን በአግባቡ ሊያከናውን አልቻለም፡፡

በመሆኑም ሰሞኑን በተደረገ ውይይት ሚድሮክ የያዛቸውን ፕሮጀክቶች እንዲነጠቅ የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሷል ብለዋል።

እንደ ኢንጂነር ፈቃዱ ገለፃ፤ከሚድሮክ የሚነጠቁት መንገዶች ከአያት  እስከ የረር ጐሮ፣ ከጉርድ ሾላ  እስከ ሲ.ኤም.ሲ / አያት ኮንዶሚኒየም እና የብሥራተ ገብርኤል መንገዶች ናቸው፡፡

እርምጃውን ለመውሰድም የአስተዳደሩ የመጨረሻ ውሳኔ እየተጠበቀ  ነው ተብሏል።

ይሁንና አል-አሙዲ-ከ አገዛዙ ሹመኞች ጋር ካላቸው ወዳጅነት እና የጥቅም ትስስር አንፃር  ባለሥልጣኑ በሚድሮክ ላይ ያስተላለፈው ፕሮጀክቶችን የመንጠቅ ውሳኔ ተግባራዊ እንዳማይሆን  ጉዳዩን በቅርበት ሚከታተሉ ወገኖች አስተያየት ሰጥተዋል።
ጋዜጣው እንዳለው ሚድሮክ፤ አዲስ አበባ ውስጥ እየገነባቸው ላሉት መንገዶች መዘግየት እንደ ምክንያት የሚያቀርበው የወሰን ማስከበር ችግርን ሲሆን፣ ባለሥልጣኑ ግን ይህን ምክንያት አይቀበለውም፡፡
ኢንጂነር ፈቃዱ ሚድሮክ በተደጋጋሚ ቢነገረው ሊሰማ አለመቻሉን ገልፀዋል።

‹‹ጩኸታችንን ፈጽሞ ሊሰማ ባለመቻሉ በጣም እያበሳጨን ነው፤›› በማለትም  ባለሥልጣኑ  በሚድሮክ መማረሩን አመልክተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአንድ ኪሎ ሜትር ከ136 ሚሊዮን ብር በላይ የተጠየቀበት ከስድስት ኪሎ ፈረንሳይ ኬላ ጉራራ መንገድ ግንባታን ለማከናወን፣ የእስራኤሉ ትድሃር የመንገድ ሥራ ተቋራጭ አሸናፊ ሆኗል፡፡

ከ4.1 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝማኔ ያለውን ይህንን መንገድ ለመገንባት የእስራኤሉ ኩባንያ አሸናፊ የሆነበት ዋጋ፤ 563.7 ሚሊዮን ብር ነው፡፡
ይህም ለአንድ ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ ከ136 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ የተጠየቀበት ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ኢንጂነር ፈቃዱ የዚህ መንገድ ግንባታ  ዋጋ ከፍተኛ  የሆነው፤ ከብር ምንዛሪ ማደግና ከኮንስትራክሽን ግብዓቶች ዋጋ መጨመር ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide