መጋቢት 1 ቀን 2004 ዓ/ ም
ኢሳት ዜና:-በጁማ ጸሎት በአወልያ ከ400 ሺ ህዝብ ያላነሱ ሙስሊሞች ተገኝተው የኮሚቴውን ውሳኔ ካደመጡ በሁዋላ አለመረጋጋት እየታየ መሆኑ ተገለጠ
ጉዳዩን በቅርብ ሆኖ የሚከታተለው ዘጋቢያችን እንደገለጠው በዛሬው እለት ሙስሊሙ የመረጣቸው ኮሚቴዎች እንደታሰሩ የሚያመለክቱ፣ ሙስሊሙ ተቃውሞውን እንዲያሰማ የሚጠይቁ መልእክቶች በሞባይል ስልክ ( ኤስ ኤም ኤስ) እና በበራሪ ወረቀቶች ሳይቀር ሲበተን አርፍዷል። ይሁን እንጅ ህዝበ ሙስሊሙ አመራሮቹ ያልታሰሩ በመሆኑ እንዲረጋጉ የሙስሊም ተወካዮች መልክቶችን ልከዋል። ድርጊቱን እየፈጸሙ ያሉት ምናልባትም ሰላማዊውን ተቃውሞ ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ለመግፋት የሚፈልጉ ሀይሎች ሊሆኑ ይችላሉ።
በትናንትናው እለት የኮሚቴው አባላት ህዝቡን ከእንግዲህ በአወሊያ እንዳይሰባሰብ እንዲመክሩ ትእዛዝ የተሰጣቸው ቢሆንም ትእዛዙን ባለመቀበል ተቃውሞዋቸውን ከህዝቡ ጋር በጋራ ሆነው ለመግፋት መወሰናቸው አስታውቀው ነበር። ዘገቢያችን እንደሚለው መንግስት በሚወስደው እርምጃ ግራ የተጋባ ይመስላል፡፤ እስካሁን በዋና ዋና አመራሮች ላይ እርምጃ ባይወስድም የአካባቢ አስተባባሪዎች የሚባሉትን አንዳንድ ሙስሊሞችም ማሰር መጀመሩን አመራሮቹ ለህዝበ ሙስሊሙ መግለጣቸው ይታወሳል።
በትናንትናው እለት አመራሩ የመንግስት ምላሽ ያልተብራራ፣ ብዥታ ያለበት፣ አፈጻጸም ላይ ችግር ሊፈጥር የሚችል እና ለሙስሊሙ ማህበረሰብ ምላሽ የማይሰጥ ነው፣ መንግስት የሙስሊም ማህበረሰቡን ገፍቶ በግልጽ ከመጅሊስና ከአህባሽ ጎን ተሰልፏል በማለት መናገራቸው ይታወሳል።
መጅሊስን በተመለከተ ምርጫ ይካሄዳል ይላል፣ ምርጫውን ማን ነው የሚያስፈጽመው፣ መቼ፣ እንዴት መልስ የለም፤ መግባባት ላይ አልተደረሰም፣ ከ19 97 ዓ.ም ጀምሮ ምርጫ ይካሄዳል እየተባለ ነበር ግን አልተተገበረም፡፡ ምርጫውን ከማህበረሰቡ የተውጣጡ ገለልተኛ ሰዎች ይምሩት ብለን አልተቀበሉንም ብለዋል፡፡
አህባሽን በተመለከተ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ ቶታል ሦስት ቁጥር ማዞሪያ የራሱን መስኪድ ከፍቶ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን ሲያሰለጥንና ሲያስተምር አልተቃወምንም ነገር ግን በመጅሊሳችንና በመስኪዶቻችን ከመንግስት ጋር ሆኖ አስተምህሮቱን ሲጭንብን ነው የተቃወምነው፡፡ የመንግስት ወኪል የሆኑት ዶ/ር ሽፈራው የእኛን ጥያቄ በአግባቡ ለማድመጥ ፈቃደኛ ባለመሆናቸውና ለአህባሽ ጥብቅና በመቆማቸውና አወሊያ የአክራሪ መፍለቂያ ነው የሚል አቋም በማራመዳቸው በአንድ ሰዓት ይጠናቀቃል የተባለው ስብሰባ ከ8 እስከ ምሽቱ 2፡30 ሰዓት ለስድስት ሰዓታት ቀጥሏል፡፡
የሙስሊሙ ማህበረሰብ የኢህአዴግ መንግሥት በሃይማኖታቸው ላይ ጣልቃ በመግባት ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች /መጅሊስ/ ጋር ተመሳጥሮ የአህባሽን አስተምህሮ በመስኪዳቸውና በተቋሞቻቸው ለማስፋፋት የሚያደርገውን ጥረት እንዲያቆም የኮሚቴ አባላት ጥያቄያቸውን እንዲያቀርብላቸው፣ ራዲዮ ፋና እና የኢትዮጵያ ራዲዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ተገቢ ያልሆነ ለመጅሊስና ለመንግስት የወገነ የፕሮፓጋንዳ ሥራ እየሰሩብን ስለሆነ መንግስት እንዲያስቆምልንና እንዲያቆምልን እንጠይቃለን በማለት አሳስበዋል፡፡
ውድ ተመልካቾቻችን በትናንትናው ዜና ኮሚቴዎቹ ለጠቅላይ ሚኒሰትሩ ጥያቄ እንዳቀረቡ ተደርጎ የተዘገበው ጥያቄ እንደሚያቀርቡ ተደርጎ እንደነበብ በአክብሮት እንጠይቃለን።
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide