ሙስሊሞች ወደ ሁዋላ መመለስ የለም አሉ

የካቲት 30 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና:-በዛሬው የጁማ ሶላት ስግደት ላይ የተሰበሰቡ ከ300-400 ሺ የሚጠጉ ሙስሊሞች መንግስት ከእንግዲህ መሰብሰብ አትችሉም ቢላቸውም፣ እነርሱ ግን ወደ ሁዋላ እንደማይሉና በጥያቄያቸው እንደሚገፉበት ገልጠዋል።

ዛሬ የኮሚቴው አባላት ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ያደረጉትን ውይይት ለህዝቡ የፋ አድርገዋል። መንግስት ጥያቄዎችን በአግባቡ አለመመለሱንም እያንዳንዱ በአወልያ የተገኘው ሙስሊም ተረድቷል። መንግስት ከእንግዲህ ወዲያ በአወልያ መስጂድ የሚደረገው መሰባሰብ እንዳይቀጥል ፣ ቢቀጥል የኮሚቴው አባላት ሀላፊነቱን እንደሚወስዱ ማስፈራራቱንም እያንዳንዱ በአወልያ የተሰባሰበው ሙስሊም ተገንዝቦአል። የፌደራል ሚኒሰትሩ ሰዎች እንደማይታሰሩ ቃል የገቡ ቢሆንም ከሰኞ ጀምሮ በርካታ ሰዎች ታስረዋል። ኡስታዝ አቡበክር የመንግስት መልስ ዙሪያ ጥምጥም የሚሄድ ፣ ምለሻ ብዥታ ያለበት እና ጥልቅ ማብራሪያ የሚጠይቅ ነገር ነው ሲሉ ገልጠዋል። ኡስታዙ ፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ውይይቱን ወደ ሌላ አቅጣጫ ለመውሰድ መሞከራቸውንም ገልጠዋል። ጉዳያቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማቅረባቸውን ገልጠዋል።

በመንግስት መልስ የተናደዱት ሙስሊሞች ግን ከእንግዲህ ወደ ሁዋላ ዞረን የምናይበት ምክንያት አይኖርም፣ ጥያቄያችንን ወደ ፊት እንገፋለን በማለት ተናግረዋል። አንድ ስሟ እንዳይገለጥ የፈለገች የ18 አመት ወጣት፣ መንግስት የፈለገውን ቢል በሚቀጥለው አርብም መሰብሰባችንን አናቆምም ብላለች። ጥያቄው የመብት ጥያቄ ነው ያለቸው ወጣት፣ መንግስት የፈለገውን ቢል እኛ ወደ ፊት እንጅ ወደ ሁዋላ የምንል አይደለንም ስትል አክላለች።

ማንኛውንም ትእዛዝ ከአመራሩ እንደምትጠብቅ የተናገረችው ወጣቷ፣ ወጣቱ በስሜት ብዙ ነገሮችን ለማድረግ ሲገፋፋ አመራሮቹ እንድንረጋጋ ያደርጉናል፣ አሁንም መሪዎች የሚያሳዩንን መንገድ እንከተላለን ብላለች። መንግስት በሚቀጥለው ሳምንት ስብሰባ አይኖርም እያለ ነው ሙስሊሞቹ ግን መብታችንን እናስከብራለን እያሉ ነው። በዚህ ሳምንት ውስጥ እስር ና ምናልባትም በአንዳንድ አካባቢዎች መለስተኛ ግጭቶች ሊፈጠሩ እንደሚችል ዘጋቢያችን አሁን ያለውን ውጥረት ተመልክቶ የራሱን አስተያየት አስፍሯል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide