ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በኑር መስኪድ ደማቅ ተቃውሞ አደረጉ

ግንቦት ፳፪(ሃያ ሁለት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የሙስሊም የድምጻችን ይሰማ የመፍትሄ አፈላላጊ የኮሚቴ አባላት በፍትህ እጦት በእስር ቤት መሰቃየት መቀጠላቸውን በመቃወም በአዲስ አበባ በኑር መስጊድ በተደረገው ተቃውሞ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ህዝብ መገኘቱን ዘጋቢያችን ገልጻለች።

ድምጻችን ይሰማ ቀደም ብሎ ባወጣው መግለጫ የተቃውሞው ዋና አላማ የሙስሊሙን ህዝብ ጥያቄ አንግበው በመያዛቸው በእስር እየተሰቃዩ ለሚገኙት መሪዎች ድጋፍ ለመግለጽ ነው መሆኑን ጠቅሷል።

በዘገየ ፍትህና በችሎት ድራማ እየተንከራተቱ የሚገኙት መሪዎች ሲታገሉለት እና ለእስር የተዳረጉበት አላማ የሙስሊም ህዝብ መሰረታዊ የመብት ጥያቄ አካል መሆኑን የገለጸው ድምጻችን ይሰማ፣ የእነሱ መስዋትነት ለህዝቡ የሰጡትን ቦታ፣ ለሃይማኖታቸው ያላቸውን ቀናኢነት ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው ብሎአል።

ሙስሊም ኢትዮጵያውያኑ ” ኮሚቴው የህዝብ ነው፤ እኛም ኮሚቴው ነን፣ ፍትህ ለወኪሎቻችን ” የሚሉ መፈክሮች ከፍ አድርገው በመያዝ እንዲሁም እጆቻቸውን አጣምረው በመቆም፣ የመሪዎቻቸውን ስቃይ ከመጋራት አልፈው ከጎናቸው መቆማቸውን አመልክተዋል።

የመፍትሄ አፈላላጊ የኮሚቴ አባላት የፍርድ ሂደት እንደቀጠለ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ መንግስት አባላቱን በሽብረተኝነት ለመክሰስ የሚያስችለው ይህ ነው የተባለ ማስረጃ ሊያገኝ አለመቻሉን የፍርድ ሂደቱን የሚከታተሉ ሰዎች ይገልጻሉ።

አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ የሙስሊሞችን የመብት ጥያቄ ለማዳከም መቻላቸውን አስመልክቶ በአንድ ወቅት መግለጫ የሰጡ ቢሆንም፣ ድምጻችን ይሰማ አሁንም ጠንካራ ደጋፊዎች እንዳሉት የሚያሳይ ተቃውሞ እየተካሄደ ነው።

ተቃውሞው ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ አንዳንድ የክልል ከተሞችም መካሄዱን ለማወቅ ተችሎአል።