ሙስሊም ኢትዮጵያውያን በነገው ኢድ-አል አድሃ ላይ ተቃውሞ እንደሚያሰሙ ታወቀ

ጥቅምት (አራት)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-ለወራት ተቋርጦ የነበረው የድምጻችን ይሰማ ተቃውሞ ነገ በመንግስት ባለስልጣናትና በመጅሊስ መሪዎች ንግግር ላይ ተግባራዊ እንደሚሆን ከወጣው መርሀግብር ለማወቅ ተችሎአል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም በሚካሄደው ዝግጅት የመንግስት ባለስልጣናትም ሆኑ የመጅሊስ አመራሮች ንግግር የሚያደርጉ ከሆነ ንግግሩ እስኪቆም ድረስ ተቃውሞው ይቀጥላል።

ተቃውሞው በመላ አገሪቱ እንደሚከናወን ድምጻችን ይሰማ ያወጣው መረጃ ያመለክታል።

ፖሊስ ጸጥታ ለማስከበር ዝግጅት ማድረጉን የፌደራል ፖሊስ ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል። ላለፉት ሁለት አመታት መንግስትን ከፍተኛ ስጋት ላይ ጥሎት የነበረው የድምጻችን ይሰማ እንቅስቃሴ፣ የጸጥታ ሀይሎች እርምጃ ከወሰዱ በሁዋላ ለተወሰኑ ጊዜያት ጋብ ብሎ መቆየቱ ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በዛሬው እለት በወልድያ መስጊዶች ላይ በተንጠለጠሉ ማይክራፎኖች የመንግስት ባለስልጣናት የመልካም ምኞች መግለጫ ሲያስተላልፉ ውለዋል። በኢትዮጵያ የእስልምና ታሪክ ታይቶ አይታወቅም ያሉት ነዋሪዎች፣ ማይክራፎኖቹ የአዛን ወይም የጥሪ ማስተላለፊያ እንጅ የመንግስት ባለስልጣናት የመልካም ምኞት መግለጫዎች አይደሉም ብለዋል። በሀሉም መስጊዶች ” የወልድያ ምክር ቤት እንኳን ለኢድ አል አድሀ በአል በሰላም አደረሳችሁ” ብሎአል እየተባለ መልእክት ሲተላለፍ መዋሉን ግራ የተጋቡ ነዋሪዎች ገልጸዋል።