ጥር 19 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) የከተማን ቦታ በሊዝ ስለመያዝ የወጣውን ዓዋጅ ቁጥር 721/2004 በመቃወም ዛሬ አርብ ረፋዱ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ በጽ/ቤቱ ውስጥ ለሀገር ቤትና ለውጭ ጋዜጠኞች ሰጥቷል፡፡
የመድረክ የአመራር አባላት ዶ/ር ሞጋ ፍሪሳ፣ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ አቶ ገብሩ አስራት፣ አቶ ገብሩ ገብረማርያም እና ሌሎችም ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ሰጥተዋል፡፡
የኢህአዴግ ካድሬዎች ከምንም ነገር በላይ ገንዘብ እንዴት እንደሚሰበሰብ ያውቃሉ ያሉት ዶ/ር መረራ ጉዲና ከዚህ ቀደም በግላቸው መሬት ሲቸበችቡ ነበር፤ አሁን ደግሞ የገንዘብ ፍላጎቱን ማሟላት ያቃተው የኢህአዴግ መንግሥት የአዲስ የመሬት አዋጅ አውጥቶ ዜጎችን እያደኸየ ሃብት በመንጠቅ ኢኮኖሚውንና ፖለቲካውን በሞኖፖል ተቆጣጥሮ እየለመኑት እንዲኖሩና ዘወትር እንዲቆጣጠራቸው ይፈልጋል፡፡
በፊውዳሉ ጊዜ እንደነበረው የኢህአዴግ መንግሥት ዜጎችን ከአካባቢያቸው ሲያፈናቅል ብትፈልጉ ጣራና ግርግዳውን ሸጣችሁ ሂዱ፣ መሬቱ የመንግሥት ነው እያለ ያሾፍባቸዋል የደርግ መንግሥት እንኳ ይሄን አላደረገም፣ እንደውም ሰው ከባንክ ብድር እየወሰደ ቤት እንዲሰራ ያመቻች ነበር እንጂ ጣራና ግርግዳ ነው የእናንተ እያለ ዜጎችን አላፈናቀለም፡፡ ምክንያቱም ሰው ቤቱን የሚሰራው መሬት ላይ ነው እንጂ አየር ላይ አይደለም፤ የቤት ባለቤትነት ከመሬት ተነጥሎ አይታይም፤ ኢህአዴግ ግን ዜጎችን ሃብታቸውን እየነጠቀና እያደኸየ ሰጪና ቀሚ ሆኖ ነው መግዛት የሚፈልገው፣ ስለዚህም ይሄን የመሬት ዓዋጅ መድረክ ይቃወመዋል፡፡ አንድ ትውልድ መሬት ላራሹ ሲል ነበር የታገለው ኢህአዴግ ግን መሬት ለኢንቨስተሩ በሚል ለውጦታል ብለዋል፡፡
አቶ ገብሩ አስራት በበኩላቸው ኢህአዴግ የሕዝብን መብት እኔ እወስናለሁ ነው የሚለው የሚገርመው ነገር መንግሥትና ሕዝብ አንድ አይደሉም፣ ይህ የአመለካከት ችግር ነው፤ ምክንያቱም ሕዝብ ሲኖር እንደ ግለሰብም ነው፣ ይህን ነው ኢህአዴግም እየጣሰ ያለውና ሕዝቡን በሀገሩ የመንግሥት ጭሰኛ ያደረገው፡፡ የመሬት የባለቤትነት የይዞታ መብት ለገበሬውም ሆነ ለከተማው ሰው ሊከበርለት ይገባል፡፡ ዜጎች ባፈሩት ሃብት- ቤት የመሸጥ፣ የመለወጥ መብት አላቸው፡፡ ቤት አየር ላይ ይሰራ ይመስል መሬቱ የኔ ነው ጣራና ግርግዳ ነው የእናንተ የሚለው ሕዝብን ወደ ድህነት በመክተት በአንድ ለአምስት በመጠርነፍ እያደራጀ እንደ ሊቀመንበር እየሆነ ቤተሰብ ውስጥ ሁሉ ገብቷል፡፡ ኢህአዴግ ኢኮኖሚውን ስቆጣጠር ነው ፖለቲካውን የምቆጣጠረው ብሎ ያስባል፡፡ ከምርጫ 97 በኋላ ያወጣቸው አዋጆች በሙሉ በዚህ ቅኝት የተቃኙ ናቸው፡፡ በዚህም ላይ የመሬት አዋጁ ሃብታም ካልሆነ በስተቀር ደሃ ቤት አይሰራም የሚል አንድምታ አለው፤ ደሃዎችን የበለጠ የሚያደኸይ ነው ብለዋል፡፡
ዶ/ር ሞጋ ፍሪሳ በሰጡት መልስ መሬት ሁልጊዜ ከነፃነት ጋር የተያያዘ ነው፤ የአድዋ፣ የማይጨውም የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት የተደረገው መሬትን ለማስከበር፣ ንብረትነትን ለማረጋገጥ ነው፤ አፍሪካዊያን ቅኝ የተገዙት መሬታቸውን በመነጠቃቸው ነው፡፡ ለዚህም ነው ታግለው ያስለቀቁት፡፡ አሁን መልኩን ቀይሮ በኢንቨስተሮች ሥም ከድሆች ላይ መሬት እየተነጠቀ ነው፡፡
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ደግሞ ይሄ የመሬት ዓዋጅ ሲወጣ ህዝብ አልተወያየበትም፣ በጥድፊያ መንግሥት በጉልበት በህዝቡ ላይ ተግባራዊ ያደረገው ነው፤ ስለዚህ ከተፈጻሚነቱ በፊት ህዝብን አወያይቶ አስፈላጊም ከሆነ ህዝበ ውሳኔ (ሪፍረንደም) መካሄድ ነበረበት ብለዋል፡፡