ታህሳስ 14 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በመንግስት ከፍተኛ በጀት ተመድቦላቸው እና ስልጠና ተሰጥቶአቸው የሚንቀሳቀሱት የአህባሽ የእስልምና አስተምሮ ተከታዮች የሌሎች አስተምህሮ ተከታዮችን ለማጥፋት ሰፊ ዘመቻ በማካሄድ ላይ መሆናቸውን የተለያዩ የእስልምና አስትምህሮ ተከታዮች ለኢሳት ገልጠዋል።
በአማራ ክልል በባህርዳር ከተማ መንግስት አሰልጥኖ ያሰማራቸው የአህባሽ ተከታዮች የአልሱና እምነት ተከታዮችን ለማጥፋት ዘመቻ መክፈታቸውን በአደባባይ ሲናገሩ መሰማቱን አንዳንድ ሙስሊሞች ለኢሳት ተናግረዋል።
የአህባሽ ተከታዮች ጥቅምት 1 ቀን በደቡብ ጎንደር ወረታ ከተማ ውሀ ልማት መስሪያ ቤት አዳራሽ ውስጥ ተሰብስበው በከተማዋ ውስጥ የሚገኙትን የአል ሱና እምነት ተከታዮች ለማጥፋት መማማላቸውን የአካባቢው ሰዎች ተናግረዋል።
ወረታ ከተማ ውስጥ የአል ሱና ተከታይና አስተባባሪ ተደርገው የሚታወቁት አቶ የሱፍ ሙሀመድ ጥቅምት ስድስት ቀን ከምሽቱ አንድ ሰአት ላይ ላይ በመጥረቢያ ተመትተው መገኘታቸውን ከቤተሰቦቻቸው ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
ግለሰቡ አል ሱናን በመተው ወደ አህባሽ እንዲቀላቀሉ ከአህባሽ እምነት ተከታዮች ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸው ቆይቷል።
አቶ የሱፍ ከአህባሽ ተከታዮች ጋር ውይይት እንዲያደርጉ በተጠየቁበት ወቅት ኪታብ ወጥቶ አባቶቻችን ባሉበት ውይይት ይደረግ የሚል አቋም ማንጸባረቃቸውን ቤተሰቦቻቸው ለኢሳት ተናግረዋል።
ግለሰቡ እንደተገደለ የአካባቢው ፖሊሶች ወዲያኑ አለመድረሳቸውን የገለጡት ቤተሰቦች፣ ከደረሱም በሁዋላ እንኳን አስከሬኑ ተነክቷል በሚል ሰበብ የአስከሬን ምርመራ ሳይደረግለት ቀርቷል ብለዋል።
ፖሊስ ከሳምንት በፊት ጀምሮ የአህባሽ ተከታዮች በሳምንቱ ውስጥ ደም ይፈሳል እያሉ ሲናገሩ እንደነበር መረጃ ቢደርሰውም፣ ወገናዊ በመሆን እርምጃ አለመውሰዱን ቤተሰቦቹ ይናገራሉ።
በሰሜን ወሎም እና በምእራብ ጎጃም አካባቢም በአህባሽና በሌሎች የእምነቱ ተከታዮች መካከል ከፍተኛ ውጥረት መኖሩን የደረሰን መረጃ አመልክቷል።
ይህን ተከትሎም የአማራ የሀይማኖት የምክክር መድረክ ጉባኤ በባህርዳር ተካሂዷል።
ጉባኤው “ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢ የግል ጥቅማቸውን በሃይማኖት ሽፋን ለማራመድ የሚንቀሳቀሱ ፀረ- ሰላም ኃይሎች መስተዋላቸውን በማመልከት የየዕምነት ተቋማት መሪዎች እነዚህን የጥፋት ኃይሎች በአስተምህሮ መርሆዎቻቸው በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንዳይኖራቸው ተግተው ለመስራት ቃል መግባታቸውን በወጣው” መግለጫ አመልክቷል፡፡
እያንዳንዱ የእምነት ተቋም ለተከታይ አማኞቻቸው ትምህርት የሚሰጡ ሰባኪዎችና ዳኢዎች ከየሀይማኖት ተቋሞቻቸው የማስተማሪያ ፈቃድ ማግኘታቸውን የሚያረጋግጥ መታወቂያ መያዝ እንዳለባቸው ጉባኤው ስምምነት ላይ መድረሱም ታውቋል፡
የአማራ ክልል አስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ደሴ አሰሜ የእምነት ተቋማት በሰላም ጉዳይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ አሳስበዋል።
መንግስት አንዱን አስተምሮ በመደገፍ ያሳየው አቋም ችግሩ እየተካረረ እንደሚጣ እንዳደረገው በርካታ ሙስሊሞች ይስማሙበታል።
በውጭ አገር የሚኖሩ ሙስሊሞች መንግስት ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል የእስልምና እምነት ተከታዮችን ለመከፋፈል የሚያደርገውን ሙከራ ሲያወግዙ ቆይተዋል።
ሰሞኑን ጅዳ ሳኡዲ አረብያ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ውስጥ የዲያስፖራ ፖሊሲን ለማወያየት በተጠራ ስብሰባ ሙስሊሞች "መንግስት በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ በመግባት በኢትዮዽያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ውስጥ ሙስሊሙን የማይወክሉ ካድሬዎችን ማስቀመጡንና ከሊባኖስ ባስመጣው አዲስ ሃይማኖት ምክንያት የገጠመውን ተቃውሞ ለማብረድ በሚል ከቱርክ በእስልምና
ስም ሌላ ሃይማኖት ለማምጣት ማቀዱን” ከስፍራው የደረሰን ዜና አመልክቷል።