የፍትህ ጋዜጠኞችን ማዋከብ ቀጥሏል

ቅዳሜ ታህሳስ 14 ቀን 2004 ዓ/ም

ኢሳት ዜና፡- የሳምንታዊው ፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ፣ የጋዜጣው አዘጋጆች፣ ሪፖርተሮች እና የጋዜጣው ሠራተኞች ከዛሬ 7፡00 ሰዓት ጀምሮ ጠንከር ወዳለ ሁለተኛ ዙር የደህንነት ሠራተኞች ክትትልና ቁጥጥር ሥር መውደቃቸውን የጋዜጣው ምንጮቻችን አስታወቁ፡፡

የሣምንታዊው ፖለቲካዊ ፍትህ ጋዜጣ ባልደረቦች ከዕረቡ ታህሳስ 11 ቀን 2004 ዓ.ም ከሰሃት በኋላ ጀምሮ የጋዜጣው ቢሮ እና ቀበና አካባቢ የሚገኘው የዋና አዘጋጁ  ተመስጌን ደሳለኝ የመኖሪያ ቤት በደህንነት ሠራተኞች የቅርብ ክትትል ሥር የወደቀ ሲሆን ትላንት ዓርብ ታህሳስ 13 ቀን 2004 ዓ.ም የጋዜጣው የመጨረሻ ሥራ በሚከናወንበት ጊዜ የቢሮ አካባቢ ብቻ ተመርጦ መብራት የጠፋ ሲሆን የፍትህ ጋዜጣ ባልደረቦች ለሥራ የሚያስፈልጋቸውን ተንቀሳቃሽ የሥራ መሳሪያዎቻቸውን ይዘው መብራት ወዳለበት ወደ ተውሶ ቢሮ ሲያመሩ ሁሉ ከአሥር የማያንሱ የደህንነት ሠራተኞች በሦስት የተለያዩ መኪኖች ሆነው አጀባቸው አልተለያቸውም ሲሉ ምንጮቻችን ገልጸውልናል፡፡

ከረቡዕ ጀምሮ በውጥረት ሥር ያሉት የፍትህ ጋዜጣ ባልደረቦች በመጨረሻ ቀን ሆን ተብሎ የመብራት አገልግሎት እንዲያጡ በመደረጉ እንደምንም ሥራዎቻቸውን አጠናቀው ከምሽቱ አራት ሰዓት ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ለህትመት ቢገቡም  ድርጅቱ ማሽን ተበላሽቷል፣ ማሽን ነክሷል በሚል ሰበብ እንደወትሮው ባለማተማቸው ትንሽ ቀደም ብሎ የተጠናቀቀው አዲስ አድማስን ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ላይ ለንባብ በቅቷል፤ ፍትህ ጋዜጣም ከእኩለ ቀን በኋላ መታተም በመጀመሩ የፍትህ ባልደረቦች ጋዜጣው ለእሁድ ንባብ እንዲውል ተስማምተዋል፡፡

የፍትህ ጋዜጣ ባልደረቦች ዘወትር ጋዜጣቸው ስትወጣ ምሳ በጋራ የመብላትና የመነጋገር ልማድ እንዳላቸው የነገሩን አንድ የጋዜጣው ባልደረባ ዛሬም ከሰዓት በኋላ እንደቀድሞው ሲሰባሰቡ ከሰሞኑ ከፍ ያለ የደህንነት ሠራተኞች ቁጥርና ከአንድኛው ደህንነት በቀር ሁሉም ተቀይረው በሚገቡበትና በሚወጡበት አካባቢ ሁላ በመኪና እና በእግር በመንቀሳቀስ አእምሯቸውን ለመረበሽና ለማስጨነቅ ሲንቀሳቀሱ ውለው አምሽተዋል ብለውናል፡፡