(ኢሳት ዲሲ–ጥቅምት 20/2011)መንግስት የሕዝቡን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ እንቅስቃሴዎችን እንደማይታገስ አቶ ለማ መገርሳ አስጠነቀቁ።
በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ መግለጫ የሰጡት የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ በምዕራብ ኦሮሚያ ዞንና በቄለም ወለጋ በኦነግ ስም ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት በአፋጣኝ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በበኩሉ ዛሬ ባወጣው መግለጫ መንግስት በሕዝባችን ላይ ከፍተኛ የሰራዊት ሃይል በማሰማራት ግድያና ዘረፋ እየፈጸመ ነው ሲል ከሷል።
በሃይል የሚገኝ መፍትሔ የለም ሲልም አሳስቧል።
ታጣቂዎች በምዕራብ እና በደቡብ ክልል የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለማስቆም መንግስት ትጥቅ የማስፈታት ርምጃ መጀመሩ ተገጿል።
ኦነግ በቅርቡ የመለመላቸው ወጣቶችም ግንባሩን እየተቀላቀሉ መሆናቸው ተመልክቷል።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ወጣቶቹ ዘመናዊ መሳሪያ ከታጠቀና ከሰለጠነ መንግስት ሃይል ጋር የማይሆን ግጭት ውስጥ እንዳይገቡና ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ በሳምንቱ መጨረሻ ጥሪ አቅርበው ነበር።
አቶ ለማ መገርሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ዳግም በምዕራብ ኦሮሚያ ዞኖችና በቄለም ወለጋ በኦነግ ስም ታጥቀው ህዝብን ለችግር እያደረጉ ያሉ አካላት በአፋጣኝ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ አሳስበዋል።
መንግስት የህዝብን ደህንነት ለማስጠበቅና ሕገ-መንግስቱን የሚጥሱ ሃይላትን ለመከላከል ሲል እነዚህን ሃይሎች እንደማይታገስ አስታውቀዋል።
እስካሁን ሁኔታዎችን በትዕግስት ተመልክተናል። ነገር ግን የህዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል ግን ከዚህ በላይ መታገስ እንደማይቻል የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ ገልጸዋል።
ሕብረተሰቡና የሃገር ሽማግሌዎችም በዚህ ረገድ ታጣቂዎቹ ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመለሱ ያደርጉ ዘንድ ጥሪ አቅርበዋል።
በኦሮሚያ እና በቤንሻንጉል ክልል ያሉ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት የሁለቱ ክልሎች መሪዎች በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽሕፈት ቤት መነጋገራቸውንም መንግስታዊ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም የኦሮሞ ነጻነት ግንባር/ኦነግ/ ባወጣው መግለጫ በሃይል ርምጃ መፍትሄ አይገኝም ብሏል።
ካለፉት ሁለት ቀናት ጀምሮ በቄለም ወለጋና በጉጂ ዞን ያሉ ርምጃዎች እንዲቆሙም ጠይቋል።
በሰው ህይወትና በንብረት ላይ ለሚደርስ ጉዳትም ተጠያቂ ሊኖር ይገባል ሲል ኦነግ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።