ጥር ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የመንግስት ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የጋዜጦችና የመጽሔቶችን ስርጭት አስተካክላለሁ በሚል ያዘጋጀውን መጠይቅ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ለሚዲያዎችና ለአከፋፋዮች በማስሞላት ላይ ሲሆን ዋና አላማውም አንዳንድ ብቅ በማለት ላይ ያሉትን ነጻ ጋዜጦችን ለመቅጨት ያለመ ነው ተብሎአል፡፡ ከእንግሊዝ መንግስት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ የሚካሄደው ጥናት መነሻ ” የጋዜጣና መጽሔት አከፋፋዮች ሕግና ስርዓትን ባልተከተለ መልክ ስርጭቱን በመያዝ መንግስት የማይፈልጋቸውን ፕሬሶች ለማሳደግ ውሎአል” የሚል ነው፡፡ በዚሁ ጥናት ውጤት መሰረት እስከ ዛሬ በስርጭት ስራ ላይ የተሰማሩ ዋና አከፋፋዮች ከግብር ፣ታክስና ከመሳሰሉት ሕጋዊ ሁኔታዎች ጋር ተያይዞ ክስ ሊመሰረትባቸው ይችላል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ስራውንም ለአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ለመስጠት ሃሳብ መኖሩ ታውቋል፡፡
መንግስት ለፕሬሱ ያሰበ በመምሰል በተዘዋዋሪ ስርጭቱን ሳይቀር የሚቆጣጠርበትንና በአስተዳደራዊ ስልት የማይፈለጉትን ከጨዋታ ውጪ ለማድረግ አስቦ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ጠቁመዋል፡፡መጠይቁ ስለስርጭቱ ሒደት፣ ስለተመላሽ ጋዜጦችና መጽሄቶች ጉዳይ፣ በስርጭቱ ላይ ስላሉ ችግሮች የሚዳስስ ነው፡፡ ጽ/ቤቱ ለስርዓቱ አደጋ አይደሉም ብሎ ለሚገምታቸው ፕሬሶችም በቋሚነት ከመንግስት ድጎማ የሚያገኙበትን አሰራርም እያጠና መሆኑ ታውቋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት አንዳንድ የፕሬስ ውጤቶችን ከጽንፈኝነት ጋር በመያያዝ እየፈረጃቸው ሲሆን፣ በገዢው ፓርቲ ድጋፍ በሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ማህበራዊ ድረገጾች ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ደግሞ ጋዜጦቹ ከውጭ አገር በተለይም ከግንቦት7 ገንዘብ ያገኛሉ በማለት እየጻፉ ነው። መንግስት ከመጪው ምርጫ በፊት አደገኛ የሚላቸውን መጽሄቶች ለመዝጋት ማሰቡ ስጋት ላይ የጣላቸው አንዳንድ ጋዜጠኞች ተቃውሞዋቸውን እየገለጹ ነው።