ግንቦት ፫(ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከ160 ሺ በላይ ህዝብ በየወሩ እየቆጠበ ከዛሬ ነገ ቤት አገኛለሁ በሚል እየተጠባበቀ የሚገኘውን 40 በ60 ተብሎ የሚታወቀው የቤቶች ፕሮጀክት ትክክለኛ የማስተላለፊያ ጊዜ መቼ እንደሆነ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትሩ አቶ መኩሪያ ሀይሌ አለመናገራቸው ቆጣቢዎችን አስቆጥቷል።
በ2005 ዓም መጨረሻ በ40 በ60 የቤቶች ልማት መርሀግብር በመመዝገብ መንግስት በ18 ወራት ቤት ሰርቶ እንደሚያስረክብ የገባውን ቃል በማመን፣ ከ160 ሺ ተመዝጋቢዎች መካከል 11 ሺህ 800 ሰዎች ከዘመድ አዝማድ በመበደር ጭምር መቶ በመቶ ክፍያ ቢያጠናቅቁም መንግስት የገባውን ቃል አክብሮ ቤቶቹን ማስረከብ ሳይችል ቀርቶአል።
ሚኒስትሩ ለፖርላማው ባቀረቡት ሪፖርት ቀድመው ግንባታቸው የተጀመሩ ቤቶች ግንባታቸው 95 በመቶ መጠናቀቁንና በ2008 ዓም ለተጠቃሚዎች ይተላለፋሉ ከማለት በስተቀር ትክክለኛውን ጊዜ አልተናገሩም። በአሁኑ ወቅት ተጠናቀዋል የተባሉት 40 በ60 ቤቶች በሰንጋተራ እና በቃሊቲ ክራውን ሆቴል አካባቢ የሚገኙ 1ሺህ 200 ገደማ ቤቶች መሆናቸው ሌሎች ምንጮች የጠቆሙ ሲሆን ፣ እነዚህ ቤቶች መቶ በመቶ የከፈሉት ብቻ በእጣ ይተላለፉ ወይስ በየወሩ ለሚቆጥቡት ከ154 ሺህ በላይ ሰዎች በእጣ ይሰጥ የሚለው ገና ውሳኔ ባለማግኘቱ በዚህ አመት ለተጠቃሚዎች የመተላለፉ ነገር አጠራጣሪ መሆኑን ተናግረዋል።
አንድ የ40 በ60 ቤቶች ተመዝጋቢ ለዘጋቢያችን እንደገለፀው መንግስት ያለውን አምነንና ከየዘመድ አዝማዱ ገንዘብ ሰብስበን የሚጠበቅብንን የከፈልን ቢሆንም፣ በመንግስት የአፈጻጸም ችግር ለተጨማሪ ወጪ እየተዳረግን እንኩዋን ሌላው ቢቀር በወጉ ይቅርታ መጠየቅ አለመቻሉ አሳዛኝ ነው ብሎአል።
ሚኒስትሩ ለፖርላማው ሪፖርት ያቀርባሉ ሲባል ስለቤቶቹ አዲስ ነገር ይናገሩ ይሆናል በሚል መከታተላቸውን የገለፁት እኚሁ አስተያየት ሰጪ ፣ ተስፋ የሚሰጥ ነገር እንኳን አለመናገራቸው በግሌ አሳዝኖኛል ሲሉ ገልፀዋል።
40 በ60 የሚባለው የቤቶች ፕሮግራም መካከለኛ ገቢ ያላቸው ወገኖች የቤቱን ግምት 40 በመቶ ሲከፍሉ ቀሪውን 60 በመቶ ከባንኮች በመበደር የቤት ባለቤት የሚሆኑበት ፕሮግራም ነው። ሆኖም መንግስት ከፕሮግራሙ አላማ ውጪ መቶ በመቶ ለከፈሉት ብቻ ቅድሚያ እሰጣለሁ ማለቱ እስካሁን በማወዛገብ ላይ ይገኛል።