ግንቦት ፫(ሦስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ ባወጠው መግለጫ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ለደረሱትና እየደረሱ ላሉት የዜጎች በህገወጥ መንገድ መፈናቀል ተጠያቂነቱን በበታች የክልል፣ የዞን እና የወረዳ አስተዳደር አካላት ላይ በማላከክ መንግስትን ከተጠያቂነት ለማዳን መሞከር ” ተጨፈኑ ላታላችሁ” አይነት እርምጃ ነው ብሎአል።
በዜጎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰ በሁዋላ መንግስትን ከሃላፊነት ለማሸሽ የበታች አካላትን የመስዋት በግ በማድረግ የተኬደበት አቋራጭ መንገድ ተአማኒነት እና ተቀባይነት የሌለው ነው ሲል መድረክ ገልጿል።
መድረክ ቀደም ሲል በጉራ ፈርዳ ወረዳ፣ እንዲሁም በኦሮሚያና በጋምቤላ እና በሌሎችም ክልሎች ለተፈጸሙት የዜጎች መፈናቀልም ሆነ በቅርቡ በቤንሻንጉል ለተፈጸመው መፈናቀል በዋናነት ተጠያቂው መንግስት ነው ብሎአል።
ዜጎች ለበርካታ አመታት ከኖሩባቸው አካባቢዎች በማፈናቀል የሚፈጸመው ህገወጥ እርምጃ በህገመንግስቱ ላይ የሰፈረውን ሀገራችን የተቀበለቻቸውን የዜጎችን በነጻነት የመንቀሳቀስና የመኖሪያ ቦታ የመምረጥ አለማቀፍ ድንጋጌዎችን የሚጥስ በመሆኑ እንደሚያወግዘው መድረክ ገልጿለ።
ከቤንሻንጉል የተፈናቀሉት ሰዎች በተገቢው ሁኔታ ወደ ቀድሞ ኑሮአቸው እንዲመለሱ፣ ለተበተነው እና ለባከነው ንብረታቸው ካሳ እንዲከፍል፣ በከተሞች በአዲስ አበባ በቦሌ ቡልቡላ፣ በላፍቶ በትግራይ በመሆኒ፣ በአላማጣ እና በሌሎች አካባቢዎች የተወሰዱ የዜጎችን ቤቶች በድንገት የማፍረስ ህገወጥ እርምጃዎች የዜጎችን መብት የሚጥስና ክበረ ነክ በመሆኑ መታረም አለበት ብሎአል።