መጋቢት ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መስሪያ ቤት ለዲፕሎማቶች እና ለሚኒስትሮች በተሰጠው ስልጠና ላይ እንደተገለፀው እስላማዊው መጅሊስ እራሱን የመምራት አቅም አልነበረውም ተብሎአል፡፡
ቀድሞ የነበረው መጅሊስ ሰነፍ የነበረና የራሱን ትምህርት ቤት ለመምራት ብቃት ያለነበረው ነው ያሉት የመንግስት ከፍተኛው ባለስልጣን፣ መጅሊሱ ብዙ ስህተቶችን ፈጽሟል ብለዋል።
መጅሊሱ ያስመጣቸው የተለያዩ የውጭ ሰዎች ማስተማር ሲጀምሩ ወጣት ኢስላሚስቶቹ ተንጫጩ ያሉት ባለስልጣኑ፣ መንግስት በእስልምና ትምህርት ቤቶች ውስጥ ህገመንግስቱን ማስተማር ሲጀመር፣ መንግስት “አልሃባሽን ሊደግፍ” ነው በሚል ግርግር መፍጠራቸውን ገልጸዋል። በመንግስት በኩል የአያያዝ ችግሮች እንደነበሩም ባለስልጣኑ ተናግረው ደካማው መጅሊስ በምርጫ እንዲተካ መደረጉንም አብራርተዋል።
“አህባሽ የሚባል አስተምህሮ” የለም ያሉት ባለስልጣኑ፣ አህባሽ የሚባል ቢኖርም እንኳ ያመጣው መንግስት ሳይሆን መጅሊሱ ነው ብለዋል።
“ህገመንግስቱን ለማስከበር እና አገር ለመበተን የሚወሰደውን እርምጃ ለመከላከል ሲባል መንግስት የሚወስደው እርምጃ በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ መግባት ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም፣ አንገት ሊቆርጥ የመጣውን በህጋዊ መንገድ ጣቱን መቁረጥ ተገቢ ነው” ሲሉ ባለስልጣኑ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የመብታችን ይከበረንል ትግላቸውን እንደገና ለማስጀመር በእንቅስቃሴ ላይ መሆናቸው ይታወቃል። በርካታ የመፍትሄ አፈላለጊ ኮሚቴ አባላት በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ብዙዎችም በእስር ቤት ውስጥ አሰቃቂ ድብደባዎች ተፈጽሞባቸዋል።
የኮሚቴ አባላት የፍርድ ሂደት በሚቀጥለው ሃሙስ እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሎአል።