መጋቢት ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከፍተኛ ረሃብ የህዝቡን ህይወት አደጋ ውስጥ በከተተበት በዚህ ወቀት ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚወጣበት የ6 ባለስልጣናት ቤት ስራ በፍጥነት እየተሰራ ነው። የኢሳት የአዲስ አበባ ወኪል ግንባታውን በቅርብ ሄዶ ተመልክቶታል።
ለስድስት ከፍተኛ ጡረተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ለእያንዳንዳቸው በ25 ሚሊየን ብር ወጪ በስጦታ የሚለገሳቸው የመኖሪያ ቤት የሚገነባው ከህወሃት ጋር በቅርበት ይሰራሉ በሚባሉት በተክለብርሃን አምባዬ የግንባታ ድርጅት ነው።
በተለይ በረሃብ ምክንያት ከ 15 ሚሊየን ያላነሱ ወገኖችን ችግር ላይ በወደቁበት፣ በከተሞች አካባቢ ከፍተኛ ኑሮ ውድነትና የስራ አጥነት በነገሰበት፣ የመንግስት ሠራተኛው ሳይተርፈው ሌት ተቀን ቦንድ ግዛ እየተባለ ከጉሮሮው እየተነጠቀ ደመወዙ በሚቆረጥበት ወቅት ለጥቂት ባለስልጣናት ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎ ቅንጦት የመኖሪያ ቤት እየተገነባ መሆኑ መሰማቱ ጉዳዩን የተከታተሉ ነዋሪዎችን ሲያነጋገር ከርሟል።
ወኪላችን ተዘዋውሮ እንደተመለከተው፣ ከሁለት ወራት በፊት መሪ በሚባለው የአዲስ አበባ አካባቢ ገና የመሰረት ድንጋይ እየተጣለላቸው የነበሩ ስድስት ህንጻዎች በአጭር ጊዜ ከ60 በመቶ በላይ ግንባታቸው ተጠናቋል። ቤቶቹ የመዋኛ ገንዳና ሌሎችም ዘመናዊ መዝናኛዎች አሉዋቸው። እነዚህ ግንባታዎች ሲጠናቀቁ ለሌሎች ባለስልጣኖች ሁለተኛ ዙር ግንባታ ይጀመራል።
በአካባቢው የሚታዩ ቤቶች ለባላስልጣናቱ ቤት ሲባል በቅርቡ የሚፈርሱ ሲሆን፣ በአካባቢው የመንግስት ባለስጣኖች መኖሪያ ቤቶች ይገነቡባቸዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ አቶ አባዱላ ገመዳ፣ እጅግ ሰፊ በሆነ ቦታ ላይ ገመቹ የሚባል ስያሜ ያለው ሆቴል እያስገነቡ ነው። በቪዲዮ ላይ እንደሚታየው ግንባታው ከተጀመረ ወራት የተቆጠሩ ሲሆን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እህትም እንዲሁም ” ኦሬንጅ” የሚል እጅግ ዘመናዊ ሆቴል ገንብተዋል።