ሰመጉ በኦሮሚያ ተቃውሞ ያወጣው መግለጫ ሲዳሰስ

ኢሳት (መጋቢት 8 ፥ 2008)

ከህዳር ወር 2008 ዓም ጀምሮ እስካሁን በቀጠለው የኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል የተቃውሞ እንቅስቃሴ ከ342 ወረዳዎች በ33ቱ ላይ ብቻ በተደረገ ምርመራ የ103 ሟቾች ዝርዝር ይፋ ሆኗል። እናትና ልጅን ጨምሮ ከ8 ዓመት ህጻን እስከ 78 ዓመት አዛውንት በመንግስት ሃይሎች ግድያ እንደተፈጸመባቸው የሰብዓዊ መብት ጉባዔ በሳምንቱ መጀመሪያ ይፋ አድርጓል። መከላከያ ሰራዊት በተለይም የአጋዚ ክፍለ ጦርና ፌዴራል ፖሊስ በግድያው አብይ ተዋናይ መሆናቸው የተጠቀሰ ሲሆን፣ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስም በግድያው ተሳታፊ እንደነበርም ተመልክቷል።

በደንዲ ወረዳ ሰምቤላ ሼኮ በተባለ ቀበሌ ቢሰጥ በቀለ ለሊሳ እና ጫምሲሳ ጎንፋ የተባሉ የ20 እና የ18 ዓመት ወጣቶች ታህሳት 3 ቀን 2008 ዓም የገደለው ብርሃኑ ኢፋ የተባለ የአካባቢው የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ መሆኑንም ሰምጉ በሪፖርቱ አጋልጧል።

የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ፣ አሁን በመንግስት አስገዳጅነት ከስያሜው ላይ ኢትዮጵያን አንስቶ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ በሚል እንዲወሰን መደረጉ የተገለጸው ኢትዮጵያዊው የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ቡድን ሟቾቹን በስም፣ በአድራሻና በፎቶግራፍ እንዲሁም የቀብር ስፍራቸውን ጭምር በመዘርዘር ይፋ ባደረገው በዚሁ ሪፖርት 103 ሰዎች የተገድሉትት ከህዳር 2 ፥ 2008 እስከ የካቲት 12 ፥ 2008 ባሉት 100 ቀናት ውስጥ ሲሆን፣ ከዚያ በኋላ የተፈጸሙ ግድያዎች አልተካተቱም።

ይህ ሪፖርት የሚሸፍነው ከ342ቱ የኦሮሚያ ወረዳዎች በዋናነት ጉዳት ደረሰባቸው በተባሉት 33ቱን ብቻ በመሆኑ፣ በሌሎች ከ130 በሚበልጡት ወረዳዎች ላይ ምርመራና ማጣራት ለማድረግ የአቅም ውስንነት እንደገታው የሰብዓዊ መብት ጉባዔ አስታውቋል።

የሰብዓዊ መብት ጉባዔ ሰኞ መጋቢት 5 2008 እኤአ ማርች 14 ፥ 2016 አዲስ አበባ ላይ ይፋ ያደረገው መግለጫ በ35 ገጾች የተጠናከረ ሲሆን፣ የሟቾችን ፎቶግራፍም በከፊል አካቷል።

የሊበን ሜጫ ት/ቤት የአራተኛ ክፍል ተማሪና የ12 ዓመት ልጅ ከሆነው ታዳጊ ህለፈታ ኒግሳ እስከ 78 ዓመቱ አዛውንት አቶ ደረጀ ወርቅነህ ከመቶ በላይ ሰዎች በተገደሉበት ጥቃት አንዳንዶቹ በ3 ጥይት ተደብድበው መገደላቸውን፣ በወለንኮሚ ከተማ የተገደለው ደበላ ነገራ በአስረጂነት ተጠቅሷል። ከደበላ ነገራ ጋር ሲሳይ በቀለና ኩምሳ ጣፋ ምዕራብ ሸዋ ወለንኮሚ ከተማ ውስጥ የተገዱሉት በመከላከያ ሰራዊት አባላት መሆኑም በሰመጉ ሪፖርት ላይ ሰፍሯል።

የመከላከያ ሰራዊት በተለይም የአጋዚ ክፍለ ጦር አባላትና የፌዴራል ፖሊስ በዋናነት በተሰማሩበት በዚህ ጥቃት ብርሃኑ ኢፋ እና በዳዳ ነገራ የተባሉ የአካባቢው የጸጥታ ሃላፊዎችን ጨምሮ አንዳንድ የአካባቢው ባለስልጣናት በግድያው ተሳታፊ መሆናቸውንም በጊዜና በቦታ በዚሁ ሪፖርት ላይ ሰፍሯል።

በወለጋ ጊምቢ ጫንቃ በተባለ ስፍራ ወ/ሮ ሲረኒ ጉደታ እና የ28 ዓመት ልጃቸው እሸቱ ፈይሳ ሁለቱም ታህሳስ 4 ቀን 2008  በመንግስት ሃይሎች መገደላቸው ይፋ ሆኗል።

በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖችና ወረዳዎች የተሰማሩት የመንግስት ታጣቂዎች ማለትም የአጋዚ ክፍለ ጦርን ጨምሮ የመከላከያ ሰራዊት እንዲሁም የፌዴራል ፖሊስና ሌሎች የታጠቁ ሃይላት አደባባይ ላይ ያገኙትን ብቻ ሳይሆን መኖሪያ ቤታቸው ድረስ በመግባት ግድያ መፈጸማቸውን በዚሁ ሪፖርት ተዘርዝሯል።

በዚሁ ረገድ በሱሉልታ ከተማ ነዋሪዎች ነጋዴ የሆነው የ34 ዓመቱ አቶ መረተ አለሙ ታህሳስ 7 ቀን 2008 ዓም ዳኒ ጋዜቦ በተባለው የግል ሆቴሉ ውስጥ እንዳለ አጥሩን ዘለው የገቡት ታጣቂዎች ተኩሰው ካቆሰሉት በኋላ፣ በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በተመታ በሳምንቱ ታህሳስ 15 ቀን 2008 ዓም ህይወቱ ማለፉን የሰመጉ ሪፖርት ይዘረዝራል።

በተመሳሳይ ሆሮ ጉድሩ ዞን ጉድሩ ወረዳ ሮባ ታዬ ቦሩ የተባለ የጋራዥ ሰራተኛ እስራው ቦታ ድረስ በሄዱ ታጣቂዎች ህይወቱን አጥቷል።

የመንግስት ባለስልጣናት ግድያውን የሚፈጽሙት አመጽ ለማቆም እንደሆነ በተደጋጋሚ መግለጻቸውም ይታወሳል፥ ሆኖም ከተዘረዘሩትና በቤታቸውና በስራ ቦታቸው ከተገደሉት በተጨማሪ ሰላማዊ ሰልፍ ያስተባበሩ፣ ሆኖም አመጽ እንዳይፈጠር የተከለከሉ ሰላማዊ ሰዎች ሰልፉ በሰላም ከተጠናቀቀ በኋላ የተገደሉበት ሁኔታም መኖሩንም የሰመጉ ሊቀመንበር አቶ ብዙአየሁ ወንድሙ ለኢሳት በሰጡት ቃለምልልስ አስታውሰዋል።

በኦሮሚያ የተሰማራው የመንግስት ታጣቂ ሃይል ከግድያ ባሻገር ቤት ለቤት በመሄድ ሴቶችን መድፈሩን፣ ንብረት መዝረፉን፣ ይህም በተለይ በምዕራብ ሸዋ አምቦ ጀልዱና ግንደ በረት መፈጸሙንም ነዋሪዎች በዋቢነት ጠቅሶ ሰመጉ ሪፖርት አስፍሯል።

በጥይት ተደብድበው ጉዳት የደረሰባቸውን እንዲሁም በድብደባ እጅና እግራቸው እስኪሰበር በሰይፍ ጭምር ጥቃት የተፈጸመባቸውን በስምና በአድራሻ የዘረዘረው የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ በመንግስት ሃይሎች በሳንጃ የተወጋ ግለሰብ መኖሩንም አመልክቷል። የታሰሩና የደረሱበት ያልታወቁ ነዋሪዎች በሪፖርቱ አስፍሯል። አቶ ለቺሳ በሬቻ የተባለ ኢትዮጵያዊ 30 መንገደኞችን አሳፍሮ ከኮምቦልቻ ወደ ጌዶ ሲጓዝ ከነተሳፋሪው በፌዴራል ፖሊስ ከተደበደበ በኋላ ገንዘብና ስልካቸው መወሰዱን በሪፖርቱ ላይ ተመልክቷል።

በገበሬ ማህበር ጽ/ቤቶች በፖሊስ ንዑስ ጣቢያዎች፣ በገበሬዎች ማሰልጣኛ ጣቢያ፣ በአንድ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡስ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ከሪፖርቱ መረዳት ተችሏል።

የዳንጎቴ ሲሚንቶ ፋብሪካ ከ10 በላይ ተሽከርካሪዎች እንደተቃጠሉም ተመልክቷል።

በግንደበረት ሶስት ፖሊሶች መገደላቸውን፣ በስምና በማዕረግ ያስቀመጠው የሰመጉ መግለጫ፣ ገዳዮቹ ማን እንደሆኑ ግን አልጠቀሰም። የተገደሉት ፖሊሶች ዋና ኢንስፔክተር ዲባባ ወየሳ፣ ሳጅን ታደሰ ጀንበሬ እና ዋና ሳጅን ወገኔ ደበላ ናቸው።

ማን እንዳቃጠለው ግልጽ ባልሆነ መልኩ በምዕራብ አርሲ የኦሮቶዶክስ፣ የፕሮቴስታንትና የካቶሊክ ቤተክርስቲያን መቃጠሉንም አስፍሯል። በደቡብ ምዕራብ ሸዋ አማያ አካባቢ የአማሮችና የኦሮሞ ቤቶች በብዛት መቃጠላቸውን የጠቀሰው የሰመጉ መግለጫ፣ ከድርጊቱ በስተጀርባ የአካባቢው መሬት የሚፈልጉ ባለሃብቶችና የአካባቢው ባለስልጣናት ያቀነባበሩት መሆኑን በመታወቁ አሁን በአካባቢው ሰላም ሰፍኖ ሁለቱ ብሄረሰቦች የተቃጠለ ቤታቸውን በጋራ እያቀኑ መሆኑን ሰመጉ አስፍሯል።

የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ሰኞ መጋቢት 5 ቀን 2008 እኤአ ማርች 14 2016 ባወጣው በዚህ 104ኛ ልዩ መግለጫው በ33 ወረዳ ከተገደሉት 103 ኢትዮጵያውያን ባሻገር፣ 90 ያህል መታሰራቸውንና ከነዚህም ውስጥ የደረሱበት የማይታወቁ መሆናቸውን፣ 57 ሰዎች መቁሰላቸውን አስፍሯል። ይህ ሪፖርት ከህዳር 2 እስከ የካቲት 12 ባለው 100 ቀናት በ33 የኦሮሚያ ወረዳዎች ውስጥ የተፈጸመ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ ብቻ የተመሰረተ ሲሆን፣ ከየካቲት 12 በኋላ በመላው ኦሮሚያ የተካሄደ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎች፣ እንዲሁም ባለፉት 4 ወራት በሌሎች 312 የኦሮሚያ ወረዳዎች የተፈጸሙ ግድያዎችና ሌሎች ጥቃቶች በሪፖርቱ አለመካተቱን ከሰመጉ መግለጫ መረዳት ተችሏል።

ኢትዮጵያዊው የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ሰመጉ በመጨረሻም ለህዝብ ሰላማዊ ጥያቄዎች፣ ሰላማዊና ህጋዊ ምላሾች እንዲሰጥ ጠይቆ፣ የታሰሩ እንዲፈቱ፣ ለተገደሉ ካሳ እንዲከፈል፣ በሰው ህይወትና አካል እንዲሁም በንብረት ላይ ጥቃት የደረሰና ጥቃት እንዲደርስ ያዘዙ ሁሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቋል። መንግስትና ተቃዋሚ ሃይላት እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በህዝብና በሃይማኖት መካከል መተሳሰብና መከባበር እንዲኖር ይሰሩ ዘንድ ጥሪ አቅርቧል።

የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ በቀድሞ መጠሪያው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ በአንጋፋው ኢትዮጵያዊ ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያምና ሌሎች ኢትዮጵያውያን መስከረም 29 1984 የተመሰረተ ሲሆን፣ ባለፉት 24 አመታት 36 መደበኛ መግለጫዎችና 139 ልዩ መግለጫ በማውጣት በኢትዮጵያ ውስጥ ተፈጽመዋል ያላቸውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ ይፋ በማድረግ የእርምት እርምጃ እንዲወሰዱ ሲጠይቅ መቆየቱን ማወቅ ተችሏል።