የካቲት 26 ቀን 2004 ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአወሊያ የተሰባሰቡት የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ላቀረቡት የመብት ጥያቄ መንግስት ለህዝቡ ተወካዮች፣ ዛሬ የካቲት 26 ቀን 2004 ዓም መልስ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቅ ነበር። ምንም እንኳ መንግስት የሰጠው መልስ በይፋ ለህዝብ ባይገለጠም መልሱ አውንታዊ አይደለም በሚል ህዝበ ሙስሊሙ እየተነጋገረበት ነው። መንግስት መጅሊሱ መጠነኛ ተሀድሶ ተደርጎለት እንዲቀጥልና የአህባሽ አስተምህሮ በመጂሊሱ የተደገፈ በመሆኑ እምነቱን የማስፋፋቱ እንቅስቃሴ መቆም የለበትም የሚል አቋም እንዳለው መረጃዎች ያመለክታሉ። የመንግስትን ትክክለኛ አቋም ለማወቅ የግድ አርብን ጠብቆ ከተወካዮቹ አፍ መስማት ግድ ይላል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአህባሽን አስተምህሮ በግድ በላያችን ላይ ሊጭን የሚሞክረው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጽ/ቤት (መጅሊስ) የኢህአዴግ መንግሥት እንጂ የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ወኪል አይደለም ሲሉ የሙስሊሙ ማህበረሰብ በአወሊያ መስኪድ ከመረጣቸው ኮሚቴዎች አንዱ ዑላማ ለሪፖርተራችን ገልጸዋል፡፡
የመንግሥትን ውሳኔ እንዳለ በመጪው ዓርብ (ጁምዓ) በአስኮ መንገድ ዊንጌትን አለፍ ብሎ በሚገኘው አወሊያ መስኪድ ለኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ለማሳወቅና ሠላማዊ ትግሉን በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞችና ወረዳዎች ማህበረሰቡ ራሱ እንዲመራው ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን የጠቆሙት የሃይማኖት አባት ፣ ነገር ግን መንግሥት ሆን ብሎ በሃይማኖታችን ጣልቃ አትግቡብን የሚለውን የሕዝበ ሙስሊም ጥያቄውን የፖለቲካ እንደሆነ አድርጎ በራዲዮ ፋና እና በሥሩ በሚንቀሳቀሱ መገናኛ ብዙሃን በማስተጋባት ሙስሊሙን በመነጣጠል ሊወነጅለን በመንቀሳቀስ ላይ ነው ብለዋል፡፡
የሙስሊሙ ማህበረሰብ የመንግሥትን አካሄድ አውቆ መልካም መልስ ባይሰጥ እንኳ ኢህአዴግ የራሱን ሰዎች አስርጎ ብጥብጥ በመፍጠር የሠላማዊ ትግሉን አካሄድ መንግስት እንዳይቀለብሰው ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት እኚህ የሃይማኖት አባት በስህተት ከመንግሥት ጎን የቆሙ አንዳንድ ኢማሞችን አነጋግረናቸው በዲናችን ወይም ሃይማኖታችን ላይ ጥሩ መግባባት ላይ ደርሰናል፡፡ በዚህም ከሁለት ሣምንት በፊት ህዝበ ሙስሊሙን የዘለፉት ፒያሳ የሚገኘው የኑር መስኪድ ምክትል ኢማም ሸህ ሰይድ አህመድ በይፈጋ ሕዝበ ሙስሊሙን ይቅርታ ጠይቀዋል በማለት ለሪፖርተራችን ገልጸዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ከክልሎች፣ ዞኖችና ወረዳዎች የወከሏቸው ኢማሞችና ዑላማዎች የመጅሊስ ይፍረስና መንግሥት በሃይማኖታችን ጣልቃ አይግባ ሲሉ ፒቲሽን አስፈርመው በአዲስ አበባ ለሚገኘው ጊዜያዊ ኮሚቴ በአወሊያ መስኪድ በማስረከብ ላይ መሆናቸውን ምንጮች አስታወቁ፡፡
ባለፈው ዓርብ በአወሊያ መስኪድ ከመቶ ሃምሳ ሺህ በላይ የአዲስ አበባ እና አካባቢዋ ሙስሊሞች በተሰባሰቡበት የጸሎት ፕሮግራም ላይ ከስልጤ ዞን የሙስሊም ማህበረሰብ የተወከሉት ሸህ አብዱሰላም ከ25 ሺህ በላይ ሰዎችን ፒቲሽን ማስፈረማቸውን ገልጸው አህባሽ አምስቱን የዲናችን መሠረቶች ተራ በተራ እየሸረሸረብንና እየተቹብን ስለመጣ እንቃወማለን ብለዋል፡፡
ከጅማ ክፍለ ሃገር ተወክለው የመጡት ዑስታዝ አይደር በበኩላቸው የጅማ ማህበረሰብ መጅሊስን መቃወም ከጀመረ ከ 10 እስከ 15 ዓመት እንደሆነው ጠቁመው፣ በጅማ ለኦሮሚያ ክልል መንግሥት ፒቲሽን ለማስገባት ሞክረው እንዳልተሳካላቸውና ምናልባት ሰኞ እንደሚያሰገቡ በመጠቆም መጅሊስ እናንተንም እኛንም አይወክልም ብለዋል፡፡
ከተባበሩት የአረብ ኤምሬት /ዱባይ/ የመጡ የኢትዮጵያ ሙስሊም ማህበረሰብ ተወካይ የሆኑት ሸህ ሬዲዋን ሁሴን ሁላችንም በመንፈስ አወሊያ መስኪድ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ይህ ጥያቄ ፍጹም ሠላማዊና ሕገ- መንግሥታዊ መብታችን ነው በማለት ለጠቅላይ ሚንሥትር ጽ/ቤት፣ ለፌዴራል ጉዳዮች ጽ/ቤት፣ ለውጭ ጉዳይ ጽ/ቤት ደብዳቤ መጻፋቸውን አስረድተዋል፡፡
ከምሥራቅ ሀረርጌ ተወክለው የመጡት ሸህ ቶፊቅ በአወሊያ መስኪድ ለተሰባሰቡት ሙስሊሞች እንደተናገሩት እኔ የመጅሊሱ መሪ እና የኢህአዴግ ካድሬ የሆኑት ሸህ አህመዲን ሸህ አብዲላሂ መንደር ውስጥ ነው የመጣሁት፤ እመኑኝ ይህን ሰው አልመረጥነውም፣ የመንደሩ ሰው እንኳ አልመረጠውም ኢህአዴግ ነው ላያችን ላይ የሾመው በማለት ይኸው ባስፈረምኩት ፒቲሽን ላይ በተወለደበት ጨፌ አነኒ ወረዳ ወንድሙና አጎቱን ጨምረው አይወክለንም ይውረድልን በማለት 32486 ሙስሊሞች የፈረሙ ሲሆን በአጠቃላይ በምስረታቅ ሀረርጌ ደግሞ አንድ መቶ አስራ አራት ሺህ ሰዎች ፈርመዋል ብለዋል፡፡
ከመቱ ከተማ የመጡት የሙስሊሙ ማህበረሰብ ተወካይ ዑስታዝ አብድልናስር በበኩላቸው 9630 ፊርማ ማሰባሰባቸውን ገልጸው በቋንቋ ብንለያይም አንድ ነን፣ የአዲስ አበባው ኮሚቴ የእኛም ኮሚቴ አድርገን ተቀብለነዋል፤ ለወደፊቱም ከእናንተ ጋር እስከመጨረሻው እንታገላለን፣ እኛ መጅሊስን ከ1994 ጀምሮ እየታገልናቸው ነበር በማለት ያሰባሰቡትን ፊርማ ለጊዜያዊ ኮሚቴው አስረክበዋል፡፡
ከአሶሳ፣ ከደምቢዶሎ እና ከወለጋ ክፍለ ሃገሮች እና 11 ልዩ ልዩ ወረዳዎች የተወከሉት ሸህ ዑመር ቆሳ እና ሌላ አንድ ሰው በበኩላቸው ከ20 ሺህ በላይ የመጅሊስ እና የአህባሽ ተቃውሞ ፊርማ ማምጣታቸውን ገልጸው፣ የአህባሽን አስተምህሮ በህፃናትና በሴቶች ላይ መጫን በመጀመራቸው ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ ሲታገሉ መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡
ከምህራብ ሀረርጌ ተወክዬ ነው የመጣሁት ያሉት አንድ ኢማም የ115617 ሙስሊሞችን የተቃውሞ ፊርማ ለኮሚቴው ያስረከቡ ሲሆን ያልመረጥነው መጅሊስ ቀድሞም ተወካያችን አልነበረም ብለዋል፡፡
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide