መንግስት ለኢትዮጵያ የሚዲያ እድገት መዳከም ዋና ተጠያቂ ነው ተባለ

 

መስከረም (ሃያ ዘጠኝ)ቀን ፳፻፮ / ኢሳት ዜና :-በአዲስ አበባ ውይይታቸውን ያደረጉ የመንግስት እና የግሉ ዘርፍ ጋዜጠኞች ሚዲያዎቹ በመንግስት የአፈና እና የእጅ አዙር ቁጥጥር ስር የወደቁ ናቸው ብለዋል።

 

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በተካሄደው የባለሙያዎች የጥናት እና ምርምር ግኝት ስራዎች ላይ ተመርኩዞ ከባለሙያዎች ጋር በተደረገው ውይይት ላይ በቀረቡት ጽሁፎች እንደተገለፀው የኢትዩጵያ ሚዲያዎች አዲስ የሚቋቋሙትም ሆነ ነባር የሕትመት ሚዲያዎች የፋይናንስ ብቃታቸው ዝቅተኛ ነው።

 

ተወያዮች ካነሱዋቸው ችግሮች መካከል የሕትመት ዋጋ መናር አንዱ ነው፡፡ ጋዜጠኞች ጋዜጦች ከኀዳር 1998 ጀምሮ ይፋዊ ባልሆነ መንገድ ተቋርጦ የነበረው የፕሬስ ፈቃድ መሰጠት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ  በሕትመት ዋጋ ላይ በዓመት ውስጥ ሦስትና አራት ጊዜ ጭማሪ መደረጉን  አምርረው ተናግረዋል፡፡

 

ዘላቂው መፍትሔው መንግሥት ፕሬሱን እንደአጋር መመልከት መሆኑን የጠቀሰው የካፒታል ጋዜጣ ዘጋቢ ፣ተደጋጋሚ ታክሶች ከወረቀት ዋጋ ላይ የሚነሱ ከሆነ መንግስት ፕሬስን ከውድቀት ይታአደገዋል ብሎአል፡፡

 

የበቁ የጋዜጠኝነት  ማሰልጣኛ ተቋሞች  አለመኖር ለሙያው አለመዳበር ሌላው ምክንያት መሆኑም ተወስቷል።፡

 

ሚዲያውን የሚመሩት የሚዲያው ማኔጅመንት አባላት ከሙያው ጋር ብዙም ግንኙነት የሌላቸውና ብቃቱ የሚያንሳቸው መሆን ተጨማሪ ችግር ነው ሲሉ ተወያዮች አንስተዋል፡፡

 

በመንግስት ሚዲያዎች በኩል ደግሞ ከክልል እስከ ፌደራል ያሉ የመገናኛ ብዙሃን የከፍተኛ ሪፖርተር ፤አርታኢ ፤ አስተባባሪ ና ዳይሬክተር እርከኖች የሚሰጡት ሙሉ በሙሉ ለኢህአዴግ አባላትና ታማኞች ነው፡፡

 

መንግሥት ራሱን  ለግል ሚዲያው መረጃን ክፍት ለማድረግ ፍላጎት አለማሳየቱም እንዲሁ በውይይቱ ተወስቷል።

 

የቴሌቪዥንና የሬዲዮ መቀበያዎች አሁንም በኢትዮጵያ ውስጥ መጠናቸው ዝቅተኛ መሆን በመረጃ ዝውውር ላይ የራሱ የሆነ ተጽዕኖ አለው፡፡

 

4 ቴሌቪዥን ለ1000 ሰውና 193 ሬዲዮ ለ1000 ሰው በሆነበት ሀገር በትክክል መረጃ ለሰፊው ታዳሚ ይደርሳል ማለት ዘበት ነው ተብሎአል፡፡  በመረጃ እጥረት 85 ሚሊዮን  የሚኖርባት ኢትዮጵያ ከአለም የመጨረሻ ሀገር ናት ሲሉ ተወያዮች ገልጸዋል።

 

ምንም እንኳ የሬዲዮና የቴሌቭዥን አገልግሎቶች  በተለያዩ ቋንቋዎች መረጃዎችን ቢያቀርቡም  በዜና በኩል ምንጫቸው ሁሉ  መንግስት በመሆኑ አሰልቺም ሆኗል በሚል ትችት ቀርቧል።