(ኢሳት ዜና–ሕዳር 13/2010)መሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ ለመንግስት ትላልቅ ፕሮጀክቶች በብቸኝነት ሲሚንቶ ማቅረብ የቻልኩት ልዩ ሲሚንቶዎችን በብቸኝነት የማመርት በመሆኔ ነው አለ።
የኤፈርት ኩባንያ አካል የሆነው መሶቦ ሲሚንቶ ለግዙፍ ፕሮጀክቶቹ በብቸኝነት እንዲያቀርብ የተደረገው ግዙፉ የሙገር ሲሞንቶ ፋብሪካ በህወሃት ስርዓት በተለያየ መንገድ የማምረት አቅሙ እንዲዳከም ከተደረገ በኋላ መሆኑ ይታወቃል።
በህወሃት ንብረትነት የሚተዳደረው ኤፈርት ኩባንያ አካል የሆነው የመሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ በ2009 ብቻ በኢትዮጵያ ለተከናወኑ የፕሮጀክት ግንባታዎች 1 ነጥብ 8 ሚሊየን ቶን ሲሚንቶ ማቅረቡን አስታውቋል።
የፋብሪካው ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ክብረአብ ተወልደ ፋብሪካው ይህን ማድረግ በመቻሉ የኢትዮጵያን የሲሚንቶ ገበያ 23 በመቶ መቆጣጠር እንደቻለ ተናግረዋል።
መሶቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ የሃገሪቱ ትላልቅ ፕሮጀክቶች የሚፈልጉትን የሲሚንቶ አይነት በብቸኝነት ማቅረብ የቻለው የሚፈልጉትን የሲሚንቶ አይነት በብቸኝነት በማምረቱ እንደሆነ ስራ አስኪያጁ ገልጸዋል።
ለግልገል ጊቤ ቁጥር 3 የሃይድሮ ኤሌክትሪክ ግድብ ወደ 1 ሚሊየን ቶን ሲሞንቶ ማቅረብ የተቻለው በዚህ ምክንያት ነው ይላሉ።የኮንክሪት አስፋልት መንገድ በሙከራ ላይ መሆኑን በመግለጽም ጭምር።
መሶቦ ሲሚንቶ ይህን ይበል እንጂ ለፋብሪካው ስኬታማነት የህወሃት መንግስት ሙገር ሲሚንቶን በማዳከምና የማምረት አቅሙ እንዲያሽቆለቁል በማድረግ ትልቁን ሚና ተጫውቷል።
በተከታታይ የተሾሙትን የሙገር ሲሚንቶን ሁለት ስራ አስኪያጆች ያለምንም ምክንያት ዘብጥያ እንዲወርዱ ያደረገው የህወሃት መንግስት ለቦርድ ሰብሳቢነት ደግሞ አቶ ስዩም መስፍንን ሰይሞላቸው ነበር።
አቶ ስዩም መስፍን የሙገርና የኤፈርት የቦርድ ሰብሳቢ በመሆን የመሪነቱን ሚና እንዲጫወቱ ሲደረግ የሙገር ሲሚንቶን ውድቀት እንዲያበስሩና የሞሶቦ ሲሚንቶን ውጤታማነት እንዲያረጋግጡ ነው ይላሉ ጉዳዩን በጥልቀት የሚያውቁ አካላት።
እናም በሂደት የኤፈርት አካል የሆነው መሶቦ ሲሚንቶ ለትልልቅ ፕሮጀክቶች ብቻ ሳይሆን በሀገሪቱ ለተገነቡት አዳዲስ ዩኒቨርስቲዎችና ለሌሎች ጥቃቅን ስራዎች ሁሉ ምርቱን በማቅረብ የህወሃት በብቸኝነት ገበያውን የመቆጣጠር እቅድ እውን አድርገዋል ይላሉ።
የመሶቦ ሲሚንቶ የኳሪና አውቶ ጋራዥ መመሪያ ሃላፊ የሆኑት አቶ ፍስሃ አድሃኖም ፋብሪካው ለህዳሴው ግድብ ሲሚንቶ ማቅረብ የቻለው በሀገር ውስጥ ያሉ ሌሎች ፋብሪካዎች የማያመርቱትን ልዩ ሲሚንቶ በብቸኝነት ስለሚያመርት ነው ሲሉ በሌሎች አካላት የሚነሳውን የራስን ብቻ የማንገስ እቅድ ያረጋግጣሉ።
መሶቦ ሲሚንቶ በመቀሌ፣ጎንደር፣ባህርዳርና አዲስ አበባ ግዙፍ የማከፋፈያ ጣቢያዎችን በመክፈት ምርቱን በመላው ኢትዮጵያ እንዲሰራጭ አድርጓል።
የምርት መጠኑን በአምስት አመት ውስጥ ብቻ በመቶ ፐርሰንት በማሳደግ ከአንድ ሚሊየን ቶን ወደ ሁለት ሚሊየን ቶን ማሳደግ ችሏል።
ከዚህ በፊት በወጣው መረጃ መሶቦ ሲሚንቶ የሀገሪቱን የሲሚንቶ ገበያው 40 በመቶ መቆጣጠሩ ሲገልጽ አሁን ደግሞ ስራ አስኪያጁ የሀገሪቱን የሲሚንቶ ገበያ 23 በመቶ ነው የተቆጣጠረው ሲሉ ከበፊቱ የሚጣረስ መረጃ ሰጥተዋል።