የዚምባቡዌ አዲስ ፕሬዝዳንት አርብ ቃለ ማሃላ ይፈጽማሉ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 13/2010)የዚምባቡዌ አዲስ ፕሬዝዳንት የፊታችን አርብ ቃለ ማሃላ እንደሚፈጽሙ ታወቀ።

ሀገሪቱን ለ37 አመታት የገዙት ሮበርት ሙጋቤን ከስልጣን መልቀቅ ተከትሎ የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት ኤመርሰን ናንጋግዋን በፕሬዝዳንትነት ለመሾም ዝግጅት እየተደረገ ነው።

ዚምባቡዌን ለ37 አመታት የመሩት ሮበርት ሙጋቤ ትላንት ከስልጣን መልቀቅን ተከትሎ የሀገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት የሆኑትና ከሁለት ሳምንት በፊት በሙጋቤ በሙጋቤ ከስልጣኝ ተወግደው የነበሩት ኤምርሰን ናንጋግዋ በፕሬዝዳንትነት እንደሚሾሙ ከሀገሪቱ የሚወጡ መረጃዎች እያመለከቱ ነው።

ኤምርሰን ናንጋግዋ ከሁለት ሳምንት በፊት ከስልጣን ሲባረሩ የግድያ ሙከራ ተቀናብሮብኛል በሚል ከሀገር ወጥተው እንደነበር ይታወሳል።

ዛሬ ረቡዕ ወደ ሀገራቸው ይመለሳሉ ተብለው የሚጠበቁት ናንጋግዋ አርብ የፕሬዝዳንትነቱን መንበር እንደሚረከቡ ይጠበቃል።

ትላንት ዚምባቡዌያን ምሽቱን ሙሉ በዘፈን፣ በጭፈራና በፌስታ ሲያሳልፉ አድረው ከ37 አመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የዛሬውን ቀን ካለ ሙጋቤ መሪነት ተቀብለውታል።

ይህ ዜና እየተጠናቀረ ባለበት ሰአት በመቶዎች የሚቆጠሩ የናንጋግዋ ደጋፊዎች በአውሮፕላን ማረፊያ እየተጠባበቁ ሲሆን አዲሱ ፕሬዝዳንት ለዚምባቡዌያን አዲስ ምዕራፍ ይከፍታሉ ተብሎ ተስፋ እየተደረገ ነው።

በፖለቲካ ብልጣብልጥነታቸውና ተንኮለኝነታቸው “አዞ” በሚል ቅጽል ስም የሚጠሩት ኤመርሰን ናንጋግዋ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ከሀገር ውጪ ቢቆዩም ሙጋቤን ከስልጣን በማውረድ ሂደት ውስጥ ትልቁን ሚና እንደተጫወቱ ይነገራል።

ሙጋቤ ስልጣኑን ለባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤ ለማስተላለፍ ያደረጉትን ጥረትም አክሽፈዋል።

ይህንንም ለማድረግ የጦር መሪዎችንና የፓርቲያቸው ዛኑ ፒ ኤፍን ድጋፍ አግኝተዋል።

የእርሳቸውን በሙጋቤ ከስልጣን መወገድ ተከትሎ ነበር ባለፈው ሳምንት የሀገሪቱ ጦር አዛዦች በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ መፈንቅለ መንግስት በሚባል ርምጃ ሮበርት ሙጋቤን በቤት ውስጥ እስር ያዋሏቸው።

ዚምባቡዌን ከነጮች አገዛዝ ነጻ ለማውጣት ሚና ከተጫወቱት አንጋፋ ታጋዮች ውስጥ አንዱ የሆኑት ናንጋግዋ የሙጋቤ ቀኝ እጅና እቅድ አውጪ ሆነው አገልግለዋል።

አምስተኛ ብርጌድ በመባል የሚጠራውና ከሰሜን ኮሪያ ስልጠና ያገኘው ወታደራዊ ክፍል በ1980ዎቹ በተቃዋሚ ፖለቲከኞች ላይ ሽብር ሲፈጽም ናንጋግዋ ትልቅ ሚና እንደነበራቸው ቢገለጽም እሳቸው ግን ከደሙ ንጹህ ነኝ ብለዋል።

በወቅቱ ናንጋግዋ የሀገሪቱ የደህንነትና የስለላ ተቋም ሃላፊ ነበሩ።

በ5ኛው ብርጌድ በተቃዋሚዎች ላይ በተወሰደው ርምጃም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል።ናንጋግዋ ለድርጊቱ ሰራዊቱን ተጠያቂ አድርገዋል።

በሞርጋን ቫንጊራይ የሚመራውና ኤም ዲ ሲ ቲ ተብሎ የሚጠራው ዋናው የተቃዋሚ ፓርቲ በአዲሱ ፕሬዝዳንት ላይ ለጊዜው ተቃውሞውን ቢያሳይም በሚቀጥለው አመት ለሚደረገው ምርጫ ራሱን እያዘጋጀ እንደሆነ ከሲ ኤን ኤን ዘገባ ለመረዳት ተችሏል።

“ሮበርት ሙጋቤን በማስወገዳችን ደስ ብሎናል፣ያስወገድንው ግን አንድን ግለሰብ ነው።ለ37 አመት የሰፈነውን ጨቋኝ ስርአት ግን ገና አላስወገድንም” ብለዋል የፓርቲው ጸሀፊ ለሲ ኤን ኤን ሲናገሩ።

የሮበርት ሙጋቤን እጣ ፋንታ በተመለከተ አሁን ላይ በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም ፓርላማው ትላንት እሳቸውን በሕግ ለመጠየቅ እየተንደረደረ ባለበት ወቅት ሙጋቤ ስልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸውን ያበሰረውን ደብዳቤ ለአፈ ጉባኤው ማስገባታቸው ሁኔታዎችን ሙሉ ለሙሉ ቀይሯል።

ለነጻነት ተዋጊዎችና ለአዛውንቶች ትልቅ ክብር ያለው የዚምባቡዌ ህዝብ የጦር ሃይሉም ሆነ ሌሎች ባለስልጣናት ከዚህ በኋላ የ93 አመቱን የቀደሞውን ፕሬዝዳንትም ሆነ ቤተሰባቸውን በወንጀል ለመጠየቅ ፍላጎት ያላቸው አይመስልም።

በክብር ወደ ጡረታ ይሸኛሉ የሚለው ስሜት በዚምባቡዌያን ዘንድ ያዘነበለም ይመስላል።