ሰኔ ፭ ( አምስት ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በደቡብ ኦሞ ዞን ካለምንም ምትክ ቦታና ካሳ የመኖሪያ ቤቶቻቸውን እና የግጦሽ ማሳዎችን በልማት ስም መነጠቃቸውን የተቃወሙት አርብቶ አደሮች በገፍ ወደ እስር ቤቶች እየተጋዙ መሆኑን ምንጮቻችን አስታወቀዋል። በኩራዝ ስኳር ፋብሪካ አካባቢ ነዋሪ የሆኑ የሃመር፣ ጸሚያ፣ ዳሰነች፣ ናያቶም፣ ሙርሲ፣ ኤርቦሬ፣ ማና ብሄረሰብ አባላት የግፍ እስራቱ ተጠቂዎች ሆነዋል። በዞኑ በሚገኙ የወረዳ እስርቤቶችና በደቡብ ኦሞ ዞን ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ከሕግ አግባብ ውጪ ታስረው ሰቆቃ እየተፈጸማባቸው ይገኛሉ። በተለያዩ እስር ቤቶች ውስጥ ከመኖሪያ ቤታቸው ርቀው የታሰሩት ዜጎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘት እንዳይችሉም ተደርገዋል።
ለዘመናት ከኖርንበት አካባቢ በሃይል አንለቅም በማለታቸው የአካባቢውን ጸጥታ ለማደፍረስ የሞከራችሁ ጸረ ሰላም ሃይሎች የሚል ክሶችም ቀርቦባቸዋል። በቀጠናው ያለው ውጥረት አሁንም ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን የክልሉ ፖሊስ፣ ልዩ ጦር፣ ፌደራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሰራዊት በአካቢው በብዛት ተሰማርተዋል። ሕብረተሰቡን ባላሳመነ ሁኔታ የስኳር ፋብሪካው በስፍራው እንዲሰራ መደረጉ ከልማት ይልቅ የግጭት መንስኤ በመሆን ለዜጎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት እየሆነ ነው ።