መጋቢት ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:- በአዲስ አበባ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ መምህራን የአቋም መግለጫ በማውጣት እና ፒቲሽን በመፈረም ለሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት ተቃውሟቸውን በማሳወቅ ሥራቸውን በያዝ ለቀቅ ትላንት መጀመራቸውን ሪፖርተራችን ያናገራቸው መምህራን ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ፣ የክፍለ ከተማ እና የወረዳ ትምህርት ቢሮዎች መምህራኑን በስብሰባና በማስፈራራት ሊያደርጉት የነበረው የአቋም ማስቀየሪያ ፖለቲካዊ የኢህአዴግ አሻጥር አልተሳካም በማለት መምህራኑ ለዘጋቢያችን አስረድተዋል፡፡
የየትምህርት ቤቶች የአስተዳደር አካላት ሰኞ መጋቢት 17 እና ዛሬ ማክሰኞ መጋቢት 18 ቀን 2004 ዓ.ም በነበረው የጠዋት የሠራተኛ የሰዓት መቆጣጠሪያ ሊስት አያያዝ ላይ ከወትሮው ለየት ያለ ውጥረት በማስፈን በህመምና በፈቃድ የቀሩ መምህራን ሁሉ ሳይቀሩ ልክ ሥራቸውን በፈቃዳቸው እንደለቀቁ በማስመሰል አስተዳደራዊ ማስፈራሪያ በየትምህርት ቤቱ ቅጥር ጊቢ በመለጠፍ እንዲመጡ አስገድደዋል ያሉን አንድ የኮልፌ ት/ቤት ዲፓርትመንት ኃላፊ መምህራኑ ግን ጽኑ አቋም ይዘዋል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች መምህራን ባወጡት የአቋም መግለጫ ላይ “መንግሥት ለመምህራን ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም እንዲያስተካክል እና እንዲያስከብር በኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አማካኝነት ለረጅም ዓመታት ሲቀርብ መቆየቱ ይታወቃል፤ እኛም መላው መምህራን መንግሥት ጥያቄውን የመምህራንን ክብርና መብት በሚያስከብር መልኩ ሊያስተካክል እንደሚችል በማመን ሥራችንን በትጋት በማከናወን የጥያቄያችንንም ሂደት በመጠባበቅ ላይ እያለን በቅርቡ መንግሥት ጥያቄያችንን በተመለከተ ተጠንቶ የቀረበ የመምህራን የደመወዝ ጭማሪና የደረጃ እድገት፣ በሚል የመምህራንን ሙያ እና ክብር በሚነካ እና መንግሥትም ለመምህርነት ሙያ ያለውን ንቀትና ንፍገት ኢሞራላዊ በሆነ አስተሳሰብና አመራር ፍጹም ከእውነት ባፈነገጠ መንገድ የተጋነነ እና ህብረተሰቡን ያሳሳተ መረጃ በመገናኛ ብዙሃን ማሰራጨቱ ይታወቃል፡፡” የሚል አረፍተ ነገር ይገኝበታል።
መግለጫው በማያያዝም “በመሆኑም የመምህራንን ሙያ ለማስከበርና ጥቅማቸውን ለመጠበቅ ተብሎ የተሰደብንበትን መግለጫ በመቃወምእንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ መብታችንን ለማስጠበቅ እና ሙያችንን ለማስከበር በምንሰራውና በተረከብነው ትውልድን የመቅረጽ ከባድ ሀገራዊ ኃላፊነት ክፍያና ጥቅማ ጥቅም ማግኘትና የመከበር መብት እንዳለን ታውቆ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን አቋሞች አውጥናል።” ብሎአል፡
- የመምህራን ደመወዝ ሙያቸውንና ክብራቸውን ሊያስከብር በሚችል መንገድ አጥንተን ጨምረናል ተብሎ የተነገረው ፌዝና ማታለል እንዲሁም መንግሥት ለሙያው ያለውን እጅግ የወረደ ግንዛቤ የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ የ73 ብር ጭማሪ ከፍተኛ የቤት ኪራይ ግሽበት ያስከተለና መምህሩን ከእስካሁኑ በከፋ ሁናቴ ለመኖር ከመጣር ወደ አለመኖር ያስገባ መሆኑ እንዲታወቅ፤
- ተጨምሯል የተባለው 73 ብር በደመወዛችን ላይ እንዳይካተት እና መንግሥት በመገናኛ ብዙሃን የሰጠውን መግለጫ በተመለከተ በይፋ መምህራንን ይቅርታ እንዲጠይቅና ህብረተሰቡ አሁን ከጨበጠው የተሳሳተ ግንዛቤ እንዲወጣ እንዲደረግ፤
- የመምህራን ማህበር በአቋም መግለጫው ላይ የጠየቃቸው በርካታ የመብትና የእኩልነት ጥያቄዎች፣ የመምህራን ደመወዝ ከሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች ጋር የተስተካከለ ይሁን እና ሌሎችም ጥያቄዎች ተመልሷል ተብሎ የተገለጸው ጥያቄው እንጂ መልሱ መምህራንን የማይወክል የአመራሮቹ ብቻ መሆኑ እንዲታወቅ፤
- ከዚህ በፊት ለመምህራን ማህበር በየወሩ ከደመወዛችን ሲቆረጥ የነበረው 4 ብር ከመጋቢት ወር ጀምሮ እንዲቆምና እንዳይቆረጥብን አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡” በማለት አቋማቸውን ገልጸዋል፡፡
መምህራኖቹ ለአዲስ አበባ መስተዳደር የትምህርት ቢሮ ተቋማት ባስገቡት የአቋም መግለጫ ደብዳቤ ላይ እንደገለጹት የትምህርት ቤቶች አስተዳደር አካላት ከላይ የዘረዘርናቸውን አራት የአቋም መግለጫዎቻችን ለበላይ የአመራር አካላት በማስተላለፍ በግልባጭ እንዲያሳውቁንና የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎችንና የሚመለከታቸውን የአመራር አካላት ጠርቶ ጥያቄያችንን በአስቸኳይ እንዲመልሱልን አጥብቀን እንጠይቃለን ብሎአል።
ጥያቄያችን ተገቢውን መልስ ባያገኝ ሊከሰት ስለሚችለው ጉዳይ ትምህርት ቤቱ ኃላፊነቱን እንዲወጣ እያስገነዘብን፣ በትምህርት ሚንስቴር የአመራር ዝንፈት እና የአስተሳሰብ ድክመት ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው የተለዩ ተማሪዎቻችን ለማስተማር ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን ሲል አክሎአል፡፡
ነገር ግን ይህንን የመብትና የሙያ ጥያቄያችንን ከመመለስ ይልቅ በቅንነት ባለመመልከት የሀገራችን ልጆች በየበረሃውና በየመንደሩ ለዘመናት የተዋደቁለት ክቡር ዓላማ በጥቂት ስግብግብና አእምሮ- አልባ ግለሰቦች ወደሚፈልጉትና ወደሚመቻቸው የቡድንተኝነት፣ የጠባብነት፣ የትምክህተኝነትና ሽብር የመፍጠር ፍላጎት ወደሚል ስንኩል የትርጉም አቅጣጫ መውሰድና ጥያቄዎቻችንን ማላሸቅ ተገቢ አለመሆኑንና ፍጹም የመምህራን አስተሳሰብ እና አቋም አለመሆኑንም ጭምር እየገለጽን ፣ አቋማችንን አጽድቀን በየትምህርት ቤቶቻችን የተፈራረምንበትን ግልባጭ ከዚህ ደብዳቤ ጋር የአያያዝን መሆናችንን ለማሳወቅ እንወዳለን በማለት ለመንግስት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋልል፡፡
የደብዳቤው ግልባጭም፡- ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፡- ትምህርት ቢሮ፣ ከንቲባ ጽ/ቤት፣ መምህራን ማህበር፣ ለክፍለከተማ ስራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት፣ ትምህርት ጽ/ቤት፣ ለድርጅት ጉዳይ ጽ/ቤት፣ ለወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት፣ ለየትምህርት ቤቱ የሰው ኃይል አስተዳደር፣ ለተማሪዎችና ለብዙሃን መገናኛ አድርገዋል፡፡
___________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________________
ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.
ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide