ልማት ባንክ ዛሬም ድረስ በህወሃት ቁጥጥር ስር መሆኑን ምንጮች ገለጹ
( ኢሳት ዜና መስከረም 02 ቀን 2011 ዓ/ም ) ባንኩ ለአማራ ባለሃብቶች ሆን ብሎ ብድር እንዳይሰጥ እንደሚያደርግ በባንኩ ውስጥ የሚሰሩ ምንጮች ለኢሳት በላኩት ዝርዝር መረጃ አመለክተዋል።
ባንኩን ለመምራት እድል ያገኙት የልማት ባንክ ፕረዝዳንቶች፣ ምክትል ፕረዝዳንቶች እና ዳይሬክተሮች የስልጣን መሰረታቸው የተደራጁ እና በጥቅም የተሳሰሩ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና ዘራፊ ባለሀብቶች ናቸው” የሚሉት የውስጥ ምንጮች፣ ከዚህ ቀደም የህውሀት ባለስልጣናት እና የትግራይ ተወላጅ ባለሀብቶች ሙሉ ለሙሉ ባንኩን ተቆጣጥረው እንዳሻቸው ሲፈነጩበት የነበረ ሲሆን ፣ በአሁን ወቅት ባንኩን የሚዘውሩት ደግሞ የህወሀት መልእክተኛ የሆኑት የደህዴን ባለስልጣናት እና ከነኝሁ ጋር በብሄር ወይንም በሌላም መንገድ ግንኙነት ያላቸው ጥቂት የደቡብ ክልል ባለሀብቶች እና ብዛት ያላቸው የትግራይ ተወላጅ ባለሀብቶች ናቸው ይላሉ።
ባንኩ በህወሃት ቁጥጥር ስር እንዲወድቅ ያደረገውና ቀድሞው የባንኩ ፕሬዚዳንት ለነበሩት አቶ ኢሳያስ ባህረ እንዲሁም ምክትል ለነበሩት ለአቶ ተካ ይብራህ መረጃ በመሰብሰብና ጉዳይ በማስፈጸም በቡድን መሪ ደረጃ እየሰራ ያለው አቶ ሀብታሙ አስፋው አሉላ ሲሆን፣ ከአቶ አባይ ፀሀየ፣ በረከት ስምኦን፣ አርከበ አቁባይ ጋር በመሆን ቦሌ መንገድ ወሎ ሰፈር ትሕማር ሕንጻ ላይ በከተመው በፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል አማካኝነት ህወሃት ከልማት ባንክ የበለጠ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ስትራቴጂክ ዶክመንቶች ሲዘጋጁ እገዛ ማድረጉን፣ ከህወሀት ጀነራሎች እና ከደህንነቶች ጋር ግንኙነት ያለው፣ ኢፍትሀዊ አሰራርን የሚቃወሙ የባንኩን ሰራተኞች እድገት እንዳያገኙ እና ክትትል እንዲደረግባቸው የተሳሳተ መረጃ የሚሰጥ እንዲሁም በትግራይ ተወላጆች የሚዘወሩ ትላልቅ የባንኩ ተበዳሪዎች ካለምንም መዋጮ (Equity) ከባንኩ ብድር እንዲያገኙ ማድረጉን ምንጮች ይገልጻሉ።
በባንኩ ውስጥ በዳይሬክተር ደረጃ የሚሰራው አቶ አፅበሐ አባይ የተባለው ሰው ደግሞ ከአማራ ክልል የሚመጡትን የባንኩን ደንበኞች በግዴለሽነት በማስተናገድ ብድር እንዳያገኙ የሚያደርግ ሰው መሆኑን ምንጮች አክለው ይጠቅሳሉ። በጣት የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጅ የባንኩ ሰራተኞች እንዲህ አይነቱን ቡድንተኝነት ፈፅሞ የማይደግፉና ከነኝህም ግለሰቦች ጋር የማይገጥሙ መኖራቸውን ምንጮች ይገልጻሉ።
ከአማራ ክልል የሚመጡ ወይንም በአማራ ክልል ለሚቋቋሙ ፕሮጀክቶች የሚጠየቁ ብድሮች በአብዛኛው ቅጥ ባጣ ቢሮክራሲ እና በተራዘመ የብድር ሂደት የጠየቁትን ብድር ሳያገኙ ተስፋ ቆርጠው የሚተውበት አጋጣሚ ከመብዛቱ የተነሳ በአማራ ብሄር ተወላጆች ዘንድ ለልማት መነሳሳትን ማጣት እና ተስፋ መቁረጥን አስከትሏል።
በተቃራኒው ደግሞ ከትግራይ ክልል የሚመጡ ወይንም በትግራይ ተወላጆች ባለቤትነት የሚጠየቁ በአንድ ግለሰብ ወይንም በቤተሰብ ከሁለት በላይ ፕሮጀክቶች በአንድ ግዜ ብድር ተጠይቆባቸው በአጭር ግዜ የተፈቀደላቸውን የጎላ ቤተሰቦች፣ የኢፈርት፣ በሁለት ወንድማማቾች ተሳስረው በአምስት ግለሰቦች የተያዙ የእርሻ ተበዳሪዎችን ብድሮች በማንሳት ጠቅሰዋል።
በአንድ ወይንም በሁለት የወላይታ ብሄር ተወላጆች ስም፣ ማርቆስ አልታየ እና ያዕቆብ አልታየ፣ የተያዙ ነገር ግን በእጅ አዙር የቀድሞው የብሄራዊ ባንክ ገዥ እና የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ሐይለማርያም ደሳለኝ ናቸው ተብለው የሚታመኑ ብዛት ያላቸው የእርሻ እና ከእርሻ ጋር የተገናኙ የብድር ጥያቄዎችም በፍጥነት ፀድቀው ወደ ትግበራ መግባታቸውን የባንኩ ሰራተኞች ገልጸዋል፡፡
አሁን ለኢትዮጵያ ልማት ባንክ በፕረዝዳንትነት የተሾሙት አቶ ሀይለየሱስ በቀለ ከቀድሞው የብሄራዊ ባንክ ገዥ አቶ ተክለወልድ አጥናፉ እና ከቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ፣ ከአቶ ሽፈራሁ ሽጉጤ እንዲሁም ከዶ/ር አብረሀም ተከስተ እና በሀገሪቱ ውስጥ ካሉ ባለሀብቶች ጋር ከፍተኛ ቁርኝት ያላቸው ግለሰብ ሲሆኑ፣ ከዚህ በፊት በፕሬዝዳንትነት ያገለገሉበት የኮንስትራክሽን እና ቢዝነስ ባንክ በደካማ የስራ አፈጻጸም ምክንያት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር መዋሃዱንና አሁንም ተመሳሳይ የጥቅም ትስስር በመፍጠር እየሰሩ ነው።
አቶ ሃይለየሱስ በቅርቡም በባንኩ ውስጥ ለረጅም ግዜያት በተለያዩ ሀላፊነት ሲያገለግሉ የነበሩ ሁለት የባንኩ ሰራተኞች የባንኩ የረጅም ግዜ ተበዳሪ በሆነው እና ብድር በማይከፍለው አይካ አዲስ በሚባል ፕሮጀክት ላይ ነፃ አስተያየታቸውን በመግለፃቸው ሞራልን በሚነካ መንገድ ከደረጃ በታች እንዲሰሩ ካስደረጉዋቸው በሁዋላ፣ ሰራተኞቹ ተማረው ከባንኩ ለቀዋል፡፡ አቶ ሀይለየሱስ ለህወሀት ያለውን አጋርነት ለማሳየት፣ የልማት ባንክን የፕረዝዳንትነት ሹመት ባገኙ ማግስት ለጋምቤላ መሬት ወራሪዎች እና ደን መንጣሪዎች ለረጅም ግዜ ተከልክሎ የነበረውን የተጨማሪ ብድር ጥያቄን እና የብድር ክፍያ ማራዘሚያ ጥያቄን ለማፅደቅ እየጣረ መሆኑን ሰራተኞች ይገልጻሉ።
ቢ.ኤም.ኢ.ቲ ለሚባለው የባንኩ ተበዳሪ ግምቱ ከ አራት መቶ ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ አሮጌ ማሽን የተለጠጠ ብድር ለማግኘት በማሰብ ብቻ፣ ተበዳሪው እንደ ድርሻ መዋጮ ያቀረበውን ባንኩ የያዘለት ሲሆን፣ ይኸው ማሽንም በተደጋጋሚ ለተሰጠው ተጨማሪ ብድር ታሳቢ እየተደረገለት ይገኛል፡፡ ቢ.ኤም.ኢ.ቲ እንደ አይነት የድርሻ መዋጮ(Inkind Equity) ያቀረበው ያገለገለ ማሽን ከ አንድ ቢሊየን ብር በላይ በባንኩ የተገመተለት ሲሆን፣ ይህንንም የባንኩ ሰራተኞች የተጋነነ ግምት ነው በማለት በወቅቱ በመተቸታቸው ማስፈራሪያ ተደርጎባቸዋል፡፡
አቶ ሀይለየሱስ በቀለ በባንኩ ውስጥ እና ከባንኩ ውጭ በህወሀት ከተደራጁት ቡድኖች ጋር በሚስጥር አብረው መስራት መጀመራቸውን የሚገልጹት ሰራተኞች፣ በዚህ አካሄድ ባንኩ ቀድሞ ሲመሩት እንደነበረው ኮንስትራክሽን እና ቢዝነስ ባንክ ሁሉ የኢትዮጵያ ልማት ባንክንም ለውድቀት እና ለመፍረስ ሊዳረግ ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የልማት ባንክ ሃላፊዎችን ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም። በጉዳዩ ላይ ባንኩ የሚሰጠውን ምላሽ ይዘን እንቀርባለን።