ኢሳት (መጋቢት 14 ፥ 2008)
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ለሃገር ውስጥና ለውጭ ኩባንያዎች ለሰፋፊ እርሻዎች ሲሰጥ በቆየው ብድር ላይ የደረሰበትን ኪሳራ የሚያጣራ አካል ተቋቋመ።
ባንኩ ለበርካታ ኩባንያዎች በመቶ ሚሊዮን ብር የሚቆጠር ገንዘብ ቢያበድርም የሰጠው ብድር በትክክል የት እንደደረሰ እንደማይታወቅ የባንኩ ሃላፊዎች ገልጸዋል።
በተለይ በተመሳሳይ የእርሻ መሬት ላይ የተሰጡ ተደራራቢ ብድሮች በባንኩ ላይ ከፍተኛ ኪሳራን ያስከተሉ ሲሆን፣ በብድር አሰጣጡ ሂደት መንግስት ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰበት ተገልጿል።
መንግስታዊ ባንክ የደረሰበትን ኪሳራ ተከትሎ ለሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ሲሰጥ የነበረውን ብድር ባለፈው ሳምንት እንዲቆም ማድረጉ ይታወሳል።
ባንኩ በአጠቃላይ የደረሰበትን ኪሳራ የሚያጣራ ቡድን በተያዘው ሳምንት ወደ ጋምቤላ፣ ደቡብና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያቀና ሲሆን፣ ብድር የሰጣቸው ኩባንያዎች እያፈላለገ እንደሆነም ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ቁጥራቸው በትክልል ሊታወቅ ያልቻለ የህንድ ኩባንያዎች ከባንኩ ብድርን ወስደው ስራ ቢጀምሩም የወሰዱትን ብድር ሳይመልሱ ከሃገር መውጣታቸውም የኢትዮጵያ ልማንት ባንክ አረጋግጧል።
በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት የተቆጠቡት የባንኩ ሃላፊዎች ለሰፋፊ የእርሻ መሬቶች የተሰጠው ብድር ግን በትክክል የት እንደደረሰ እንደማይታወቅ ገልጸዋል።
የተለያዩ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት በኢትዮጵያ ሲካሄድ ቆይቷል ያሉት የመሬት ቅርምት በሺዎች ለሚቆጠሩ ነዋሪዎች መፈናቀል ምክንያት እንደሆነ ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።
ከእነዚሁ ተቋማት የቀረበን ቅሬታ ተከትሎም የአለም ባንክ ለሃገሪቱ ሲሰጥ የቆየው ድጋፍ ለዚሁ አላማ መዋሉን ለማረጋገጥ ገለልተኛ አካል አቋቁሞ ጥናትን ሲያካሄድ መቆየቱ ይታወቃል።
የባንኩ የገለልተኛ አካልም ባንኩ ሲሰጥ የነበረው የትምህርትና የጤና ድጋፍ ለመሬት ቅርምት ማስፈጸሚያ እንደዋለ ያረጋገጠ ሲሆን፣ የገለልተኛ ጥራቱን ውጤት ተከትሎም ባንኩ ለኢትዮጵያ በሚሰጠው ድጋፍ ላይ የማስተካከያ እርምጃን ወስዷል።
በባንኩ በኩል ለዘርፉ ድጋፍ ሲያደርገው የቆየው የብሪታኒያ መንግስት ሲሰጥ የነበረው አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ እንዲቋረጥ መወሰኑን መዘገባችን ይታወሳል።
የግብርና ኢንቨስትመንት እና የመሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በፌዴራል መንግስት በኩል ሲሰጥ የነበር መሬት እንዲቆም ወስኗል።