መስከረም ፳(ሃያ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ደልጊ ፣ሻውራ፣ ጎርጎራና ቋራን ለ70 ዓመታት በማገናኘት ያገለገለው ድልድይ በመንገድ ስራ በተፈጠረ የጥናት ችግር ቢፈርስም ተመልሶ ሊሰራ ባለመቻሉ ከፍተኛ ችግር ደርሶብናል በማለት
የጯሂት ከተማ ነዋሪዎች አማረዋል፡፡
ከጎንደር ወደ ጯሂት በሚወስደው መንገድ ላይ በጣልያን መንግስት እንደተሰራ የሚነገረው የሱዳን ገደል ድልድይ ከአራት ወራት በፊት በመፍረሱ ወላዶች፣አረጋውያንና የንግዱ ማህበረሰብ ከፍተኛ ችግር እየደረሰበት ነው ሲሉ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
የገዢው መንግስት መንገድ እሰራለሁ በማለት በተለያዩ ቦታዎች የሚጀምራቸው እንቅስቃሴዎች በተቋራጭ ድርጅቶችና በከፍተኛ አመራሩ የጥቅም ግንኙነት አማካኝነት በሚደረግ ሙሰኛነት ደረጃቸውን ላላሟሉ ተቋራጮች በመሰጠቱ ከጥናት ጉድለት
ድንገተኛ ችግሮች ሲከሰቱ ፈጥነው ባለማስተካከላቸው ህብረተሰቡ እየተጎዳ መሆኑን የተናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎች ፤ከወራት በፊት ለአካባቢው አመራሮች ቢናገሩም ‘በተገጣጣሚ ድልድይ ነገ ይሰራል፣ ሳምንት ይገጠማል’ በማለት የሽንገላ ቃላት ከመናገር
ውጭ መፍትሄ ባለማግኘት መክረማቸውን ገልጸዋል፡፡
አሁን ሙሉ በሙሉ የንግድ እንቅስቃሴ የቆመበት ሁኔታ እንዳለ የተናገሩት የጯሂት ከተማ ነዋሪ አቶ ደረሰኝ ተስፋ ፣ ወላዶችን በቃሬዛ ይዘው ወንዙን በሚሻገሩበት ጊዜ ውሃው ነፍሰ ጡሯን እናት የወሰደበት ክስተት በቅርብ ጊዜ የተፈጸመ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የጡረታ ድጎማ የሚያገኙ አረጋውያን የጡረታ አበላቸውን ለመውሰድ አንድ ቀን በእግራቸው ተጉዘው ወንዙ ላይ ሲደርሱ፣ በጡረታ ከሚያገኙት አነስተኛ ገንዝብ እስከ 60 ብር ለዋናተኞች በመክፈል እንደሚሻገሩም ተናግረዋል፡፡
ተለዋጭ አስፋልት ይሰራል ተብሎ የተጀመረው ይህ መንገድ በፈጠረው የቁፋሮና ድልደላ ስራ ድልድዩ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ችግር አስቀድሞ ባለማጥናቱ የደረሰ ችግር ነው በሚል የቀረበውን የህዝብ ቅሬታ የሚጋሩት የወረዳው አስተዳደር ጽህፈት ቤት
ሃለፊ አቶ እያዩ ውድነህ፣ መንገዱ ወደ አምስት ሜትር ከፍታ ያለው በመሆኑ ውሃው ተጠቃሎ ወደ ድልድዩ በመሄዱ የተከሰተ ችግር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለበላይ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ብናሳውቅም የተሰጠን ምላሽ ተገጣጣሚ ኮንቴነር ይመጣል በማለት
ህብረተሰቡን ከመሸንገል ውጭ እስካሁን ምንም መፍትሄ አልተሰጠም ብለዋል፡፡ሕዝቡ መጉላላት የለበትም የሚሉት የአስተዳደር ጽህፈት ቤት ሃላፊው የሚመለከተው አካል አፋጣኝ ምላሽ መስጠት አለበት በማለት ተናግረዋል፡፡