ሚያዚያ ፲፰(አሥራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ምስራቅ አፍሪቃ ካለፉት 50 ዓመት ወዲህ ባልታዬ ከፍተኛ በሆነ ድርቅ መጠቃቱን ተክቶሎ በኢትዮጵያ የረሀብተኛ ቁጥር 20 ሚሊዮን መድረሱን የመንግስታቱ ድርጅትና የዓለማቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ሪፖርት ያሳያል። ከነዚህ ተረጅዎች መካከል 8 ሚሊዮን ያህሉ ህይወታቸው በቋፍ ላይ የሚገኝ ህጻናት ናቸው።
የተረጅዎች ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ የማሻቀቡን ያህል ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ የቀረበው የእርዳታ ጥያቄ በበቂ ሁኔታ ምላሽ ሊያግኝ አለመቻሉ፤ ችግሩንና እልቂቱን ያባብሰው ይሆናል ተብሎ በተሰጋበት በአሁኑ ወቅት ፣ ለእርዳታ የመጣ የስንዴ ዱቄት ተሰርቆ ለዳቦ ቤቶች እየተሸጠ መሆኑ ተዘግቧል።
ጋዜጠኛ ተሻገር ጣሰው እንደዘገበው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ በወረዳ 6 ቀበሌ12 /13 ልዩ ስሙ ሳሪስ ዘንባባ አካባቢ ኮድ3- 00008 አአ ፒክአፕ የሆነ መኪና በትናንትናው ዕለት ከቀኑ10:00 ሰዓት ገደማ ሲሆን 20 ኩንታል የእርዳታ ስንዴ ዱቄት በሸራ ሸፍኖ በአካባቢው በሚገኝ ሳባላን ዳቦ መጋጋሪያ ቤት ሊያራግፍ ሲል ፓሊስ ጥቆማ ደርሶት ዱቄቱን በቁጥጥር ስር ሲውል በስፍራው ተገኝቶ በዐይኑ ተመልክቷል።
እንደ ጋዜጠኛው ሪፖርት የእርዳታ የስንዴ ዱቄት የጫናው የፒክአፕ መኪና አሽከርካሪ ለጊዜው የተሰወረ ሲሆን ፤ፓሊስ ዱቄቱን በአይሱዙ መኪና ጭኖ ወደ ፓሊስ ጣቢያ ለምርመራ ሲወስደው ዐይቷል::
የዳቦ መጋገሪያ ድርጅቱ በአሁኑ ሰዓት የታሸገ ሲሆን፤ ዱቄቱን ያወጣውና ሊገዛ ያሳበው ማነው? የሚለውን ለማወቅ ፓሊስ ምርመራ እያደረገ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።