በጋምቤላ የቤት ለቤት ፍተሻ በመካሄድ ላይ ነው

ሚያዚያ ፲፰(አሥራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ምንጮች እንደዘገቡት በጃዊ የስደተኞች ካምፕ ውስጥ የተደረገውን ግድያ ተከትሎ በከተማው የሚታየው ውጥረት እንዳጨመረ ሲሆን፣ ዛሬ ፖሊስ አውራ ጎዳናዎችን በመዝጋት እንዲሁም በሰዎች መኖሪያ ቤቶች በመግባት ፍተሻ ሲያደርግ ውሎአል።
የኑዌር ሱዳናውያን ከአንድ የመኪና አደጋ ጋር በተያያዘ የወሰዱት አሰቃቂ እርምጃ የ21 ኢትዮጵያውያንን ህይወት የቀጠፈ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያን ለምን ተጠቃን በሚል ስሜት የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ያደረጉት ጥረት በፖሊሶችና መካለከያ ጣልቃ ገብነት እንዲቆም ተደርጓል። ይሁን እንጅ ጥቃቱ በኢትዮጵያ ኑዌሮችም ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ገልለተኛ ታዛቢዎች ይናገራሉ። ሁኔታው እጅግ አስቸጋሪ መሆኑን የሚገልጹት ታዛቢዎች፣ የኢትዮጵያ ኑዌሮች ከደቡብ ሱዳን ኑዌሮች ጋር የሚያገናኛቸው አንዳች ነገር እንደሌለና በከተማዋ የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ይህን እንዲረዱላቸው በመጠየቅ ላይ ናቸው።
ምንም እንኳ ችግሩ ለጊዜው ረገብ ያለ ቢመስልም፣ አሁን በሚታየው ሁኔታ በማንኛውም ጊዜ ግጭት ሊከሰት ይችላል ብለው እንደሚሰጉ የከተማዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ጋምቤላ የነበሩት የደቡብ ሱዳን መንግስት ተቃዋሚ አንጃ መሪ የሆኑት ሪክ ማቻር ወደ ጁባ ተመልሰዋል። ሪክ ማቻር የሽግግር መንግስቱን የሚቀላቀሉ ሲሆን፣ምርጫ እስከሚካሄድበት ጊዜ ድረስ ተቀዳሚ ምክትል ፕ/ት ሆነው ያገለግላሉ። የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ጋምቤላ የሰፈሩት ስደተኞች ወደ አገራቸው ወዲያውኑ የሚመለሱ ይሁን አይሁን የታወቀ ነገር የለም።
በሌላ በኩል ከጋምቤላ ታግተው ስለተወሰዱት ከመቶ በላይ ኢትዮጵያውያን ሴቶችና እናቶች ሁኔታ መንግስት መግለጫ ተከታታይ ከመስጠት መቆጠቡ ብዙዎችን ግራ አጋብቶአል። ድርጊቱን በፈጸሙት የሙርሌ ጎሳ አባላት ላይ ከበባ መደረጉ በመንግስት በኩል ቢነገርንም፣ እስካሁን ድረስ ምንም ውጤት ሊታይ አልቻለም።