ኢሳት (ግንቦት 4 ፥ 2008)
የተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) የሚዘሩት ዘር ለሌላቸው ገበሬዎች ዘር እንዲቀርብላቸው የዕርዳታ ተቋማትን ተማፀነ። ድርጅቱ በድርቅ የተጠቁ ገበሬዎች ለዘር የሚሆን እህል ካላገኙ ለከፍተኛ ረሃብና የምግብ አቅርቦት ችግር እንደሚጋለጡም አስጠንቅቋል።
በረሃብ ለተጠቁ ገበሬዎች ዘር ለማከፋፈል በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ 10 ሚሊዮን ዶላር መገኘት እንዳለበትና ይህ ካልሆነ ግን የተጠቂ ቤተሰቦች ህይወታቸውን በረሃብ ምክንያት ሊያጡ ይችላሉ ሲሉ ሚስተር ድያሎ መናገራቸውን በካምፓላ የሚታተመው ኢስት አፍሪካን ቢዝነስ ዊክ የተባለ ጋዜጣ አስነብቧል።
የመኸር ወቅት የቤተሰብን የምግብ አቅርቦት ለማሻሻል እና በምግብ እራስን ለመቻል እጅግ አስፈላጊ ነው ያሉት በኢትዮጵያ የምግብና የእርሻ ድርጅት ተወካይ አማዱ አላሆርይ ዲያሎ ፣ ገበሬዎች ምርት ማምረት እንዲችሉ የዘር ስርጭት አቅርቦት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ሰብዓዊ ጉዳይ ነው በማለት የእርዳታ ድርጅቶች ለገበሬዎች ዘር እንዲያቀርቡና እንዲያከፋልፍሉ ተማፅነዋል።
ሚስተር ድያሎ እንደተናገሩት “የምግብ አቅርቦት ችግር እየባሰ ቢሄድም፣ የለጋሽ አገራት ዕርዳታ ተስፋ የሚያስቆርጥ ደረጃ ላይ ነው ያለው ካሉ በኋላ፣ የተባበሩት መንግስታት የእርሻና ምግብ ድርጅት ካቀረበው ጥሪ 15% ብቻ እርዳታ እንደተገኘ ተናግረዋል።
በተለይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ ነው ያሉት ሚስተር ድያሎ፣ በዝናብ መዘግየት እንዲሁም የዝናብ ያለጊዜው መጣል ሁኔታውን እንዳባባሰው ለመገናኛ ብዙሃን መናገራቸውን ኢስት አፍሪካን ቢዝነስ ዊክ አስነብቧል።
እንደ FAO ገለጻ የኢትዮጵያ 1/3ኛ ወይም 224 ወረዳዎች ከፍተኛ የምግብ እጥረት የሚታይባቸው አካባቢዎች ናቸው።
1.7 ሚሊዮን የሚሆኑ የገበሬ ቤተሰቦች ምንም አይነት የሚዘሩት የእርሻ ዘር የሌላቸው መሆኑን ያስታወቀው FAO፣ ከ90 ወረዳዎች ውስጥ 150,000 ቤተሰቦች ምንም አይነት የአስቸኳይ የዘር እርዳታ ያልተሰጣቸው ናቸው ብሏል። FAO ትኩረት የሰጠው እነዚህ ወረዳዎች ላይ ነው ሲሉ የተባበሩት መንግስታት የምግብና እርሻ ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ የቡድን መሪ ሚስተር ፕየሬ ቫውቲየር መናገራቸውን ኢስት አፍሪካ ቢዝነስ ዊክ በዘገባው አስፍሯል።
አብዛኞቹ ቤተሰቦች ለዘር ያስቀመጡትን እህል ባለፈው አመት በመዝራታቸውና የቀረውንም በምግብነት ስለተጠቀሙት በአሁኑ ወቅት ምንም የሚዘሩት እህል የላቸውም ተብሏል።