ለምግብ እጥረት የተጋለጡ የህጻናትና በእርግዝና ላይ እናቶች ቁጥር በእጥፍ ሊያድግ እንደሚችል ተመድ አስታወቀ

ኢሳት (ግንቦት 4 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ ተከስቶ ባለው የድርቅ አደጋ በመካከለኛ ደረጃ ለምግብ እጥረት የተጋለጡ የህጻናትና በእርግዝና ላይ እናቶች ቁጥር በእጥፍ ሊያድግ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ።

በመካከለኛ ደረጃ የተፈረጁ ህጻናትና እናቶች ቁጥር 1.7 ሚሊዮን አካባቢ ቢሆንም ይህ ቁጥር በቅርቡ ወደ 2.5 ሚሊዮን ሊያሻቅብ እንደሚችል ትንበያ መኖሩን ድርጅቱ ይፋ አድርጓል።

በሃገሪቱ ተከስቶ ባለው የድርቅ አደጋ ዙሪያ ወቅታዊ ዝርዝር ሪፖርትን ያቀረበው ድርጅቱ አፋጣኝ ለሆኑ የእርዳታ አቅርቦትም በቀጣዮቹ ስድስት ወራት 702 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግም ገልጿል።

ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ የተጋለጡ ከ10 ሚሊዮን በላይ የሃገሪቱ ዜጎች ወቅታዊ ድጋፍን ባለማግኘታቸው ሳቢያ ኣየደረሰ ያለው ጉዳት እየጨመረ መምጣቱንም ለመረዳት ተችሏል።

በቅርቡ ወደ ረሃብ ደረጃ ለመድረስ አንድ ደረጃ ብቻ የቀራቸው ወረዳዎች ቁጥር ከ186 ወደ 219 ከፍ ማለቱን ያወሳው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ከእርዳታ አቅርቦት ማጠር የተነሳ የዘይትና የጥራጥሬ አቅርቦቶች በበቂ ሁኔታ እየቀረቡ አለመሆኑንም አመልክቷል።

ከሁለት ወር በኋላትም መጠነ ሰፊ የሆነ የእርዳታ አቅርቦት መስተጓጎል በሃገሪቱ ሊከሰት እንደሚችል ትንበያ መኖሩንም ድርጅቱ አክሎ ገልጿል።

በቀጣዮቹ ስድስት ወራቶች ውስጥም ወደ 150ሺ የሚጠጉ ሰዎች በድርቁ በተጎዱ አካባቢዎች ይፈናቀላሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም ከቀያቸው የተፈናቀሉ ከ20ሺ በላይ ሰዎች ያለመጠለያ እንደሚገኙም ታውቋል።

በተለያዩ ክልሎች እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብና የጎርፍ አደጋም ድርቁን በመታደጉ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮ መቀጠሉንም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሪፖርቱ አስፍሯል።

ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ለተጋለጡ ሰዎች በቂ አለም አቀፍ ድጋፍ አለመገኘቱን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ መንግስትና አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት በለጋሽ ሃገራት በመዘዋወር ድጋፍን ሲያሰባስቡ መቆየታቸው ይታወሳል።

ይኸው በስድስት ክልሎች ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ ወደረሃብ ሊሸጋገር ይችላል የሚል ስጋት መኖሩን የሚገልጹት አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች በበኩላቸው ተረጂዎችን ለመታደግ አለም አቀፍ ርብርብ እንዲደረግ በመጠየቅ ላይ ናቸው።