አንድ የዱባይ ኩባንያ የሶማሊላንድ ወደብን ከሶማሊ ላንድ ጋር በጋራ ለማልማት ስምምነት ፈጸመ

ኢሳት (ግንቦት 4 ፥ 2008)

የኢትዮጵያ መንግስት የጎረቤት ሶማሊላንድ ወደብን ለመጠቀም ድርድር እያካሄደ ባለበት ወቅት መቀመጫውን በዱባይ ያደረገ አንድ ኩባንያ ወደቡን ከሶማሊላንድ ጋር በጋራ ለማልማት ስምምነት ፈጸመ።

የጅቡትን ወደብ እያስተዳደረ የሚገኘውና ዲፒ ወርልድ (DPWorld) የሚል መጠሪያ ያለው ኩባንያ የሶማሊላንድ ወደብን ለማስተዳደር ስምምነት መፈጸሙን ለኢትዮጵያ አማራጭን የሚያሳጣ አካሄድ እንደሆነም በጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት አስታውቀዋል።

መንግስት ከጅቡቲ ወደብ በየጊዜው የሚደረግበትን የአገልግሎት ክፍያ በመሸሽ ፊቱን በቅርቡ ወደ ሶማሊላንድ በማዞር ድርድር ሲያካሄድ መቆየቱ ይታወሳል።

ይሁንና፣ በአሁኑ ወቅት የጅቡቲ ወደብን እያስተዳደረ ያለው ኩባንያ 442 ሚሊዮን ዶላር በመመደብ ራሷን እንደ ሃገር አድርጋ ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር ወደቡን በጋራ ለማልማት ስምምነት መፈጸሙን ገልፍ ኒውስ የተሰኘ ጋዜጣ ሃሙስ ዘግቧል።

በቅርቡ በዱባይ ጉብኝትን ያደረጉ የሶማሊላንድ ባለስልጣናት ከኩባንያው ጋር ስምምነት የደረሱ ሲሆን፣ የወደቡ ልማትም ከኢትዮጵያ ጥቅምን ለማግኘት ያቀደ እንደሆነ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ መንግስት ይህንኑ ወደብ ለመጠቀም ለአመታት የቆየን ድርድር ከሶማሊላንድ ጋር ሲያካሄድ መቆየቱንም ለመረዳት ተችሏል።

ይሁንና የጅቡቲ ወደብን እያስተዳደረ ያለው ኩባንያ ሶማሊላንድ ወደብንም ጠቅልሎ መያዙ ለኢትዮጵያ “መጥፎ ዜና” መሆኑን የተለያዩ አካላት አስረድተዋል።

የሶማሊላንዱ ፕሬዚዳንት አህመድ ሞሃመድ ከቀናት በፊት በዱባይ ጉብኝትን ባደረጉ ጊዜ ከዲፒ ወርልድ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሱልጣን አህመድ ቢን ሱለይማን ጋር ስምምነት መፈራረማቸውን ገልፍ ኒውስ በዘገባው አመልክቷል።

የጅብቱ ወደብን በዋነኛነት እየተጠቀመች ያለችው ኢትዮጵያ ከወደቡ አገልግሎት ብቻ በየአመቱ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪን እንደምታደርግ ይታወቃል።