ጥቅምት ፲፬(አስራ አራት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ብርሀንና ሰላምን ለ20 አመታት የመሩት የኢህአዴግ ደጋፊ የሆኑት ወ/ሮ ሙሉወርቅ ገብረህይወት ጡረታ ወጥተው በእርሳቸው ምትክ የህወሀት አባሉ አቶ ተካ አባዲ ዛሬ ስራስኪያጅ ሆነው ተሹመዋል።
የአርቲስቲክ ማተሚያ ቤት ስራ አስኪያጅ ሆነው የቆዩት አቶ ተካ፣ ከሰራተኛው ጋር ከፍተኛ ውዝግብ ውስጥ በመግባትና በአስተዳደራቸው ብልሹነት ይታወቃሉ።
ዛሬ ከሰአት ሹመቱ ይፋ ሲሆን የብርሀንና ሰላም ሰራተኞች እና ሌሎች የአስተዳደር ሰራተኞች በድንጋጤ መዋጣቸው ተሰምቷል። ወ/ሮ ሙሉወርቅ ምንም እንኳ የኢህአዴግ ደጋፊ ቢሆኑም፣ ከሰራተኛው ጋር ተግባብተው በመስራት የተመሰገኑ ነበሩ።
በአዲስ አበባ የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ውስጥ ቁልፍ ሚና ያላቸው አቶ ተካ፣ ህገወጥ በሆነ መንገድ መሾማቸውንም ውስጥ አዋቂዎች ገልጸዋል።
የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ያቋቋመው የሰራተኛ አዋጅ 377 ስራ አስኪያጆች የሚሾመው የስራ አመራር ቦርድ መሆኑን፣ ማስታወቂያ በጋዜጣ ወጥቶ አቅም ያለው ሰው ተወዳድሮ የሚገባበት ቢሆንም፣ ማስታወቂያ ሳይወጣ፣ በኢህአዴግ ቀጥተኛ ትእዛዝ እንዲሾሙ ተድርጓል።
የስራ አመራር ቦርዱ ለልማት አጄንሲው ማስታወቂያ እንዲወጣ ደብዳቤ ቢልክም፣ በመንግስት ተጽእኖ ስር የሚገኘው ኤጀንሲ በቀጥታ አቶ ተካ እንዲሾሙ አድርጓል።
ፍትህ፣ ፍኖተ ነጻነትና ሌሎች መንግስትን ይቃወማሉ የሚባሉ ጋዜጦች በብርሀንና ሰላም መሪዎች እንዳይታተሙ መደረጉ ይታወቃል። አዲሱ ስራ አስኪያጅም ይህንኑ የመንግስት አፈና ፖሊሲ አስቀጥላሉ ተብሎ ከፍተኛ እምነት ተጥሎባቸዋል።