ለሃይማኖታዊ የሃጂ ፀሎት የሚጓዙ ምእመናን በኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ መንገላታት ደረሰባቸው።
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 08 ቀን 2010 ዓ/ም ) መነሻቸውን ከአዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ በማድረግ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተገቢውን የበረራ መስፈርቶችን አሟልተው ወደ ሳኡዲ አረቢያ ለመብረር ሲጠባበቁ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጣቸው በረራቸው እንዲሰረዝ በመደረጉ ለከፍተኛ እንግልትና ለተጨማሪ ወጪዎች ተጋላጭ ሆነዋል።
አብዛሃኞቹ እድሜያቸው የገፋ አቅመ ደካማ አዛውንቶች፣ አካል ጉዳተኞችና ህመምተኞች፣ ከክፍለ ሃገር ድረስ የመጡ የሃጂ ተጓዦች፣ የሚሄዱበት ስለሌላቸው በአየር ማረፊያው ግቢ ውስጥ በርሃብና ማረፊያ እጦት መንገላታቸውን ታውቋል። መንገደኞቹ ካለምንም በቂ ማረፊያ አልባሌ ቦታዎች ላይ በየአግዳሚው ላይ እንዲተኙ መገደዳቸው እንዳሳዘናቸው ምንጮቻችን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ዝና ያለው ብቻ ስለሆነ ሳይሆን አገራቸውንም ጭምር ለማገዝ ባላቸው ፍላጎት፤ በአገራቸው አየር መንገድ ለመብረር ምርጫ ቢያደርጉም ድርጅቱ ግን እንደ ዜጋም እንደ ደንበኛም አሳፋሪ ተግባር ፈጽሞብናል ይላሉ። በረራው አስቀድሞ መስተጓጎሉን ሊያሳውቀን ይገባ ነበር። ሳኡዲ አረቢያ ውስጥ የሚቀበሉን ዘመድና ጓደኞቻችንም እኛን በመጠበቅ አብረውን እየተንገላቱ ነው። የተጀመረው ለውጥ እውን እንዲሆን መንግስት አየር መንገዱ ውስጥ ያለውን ኢፍትሃዊ አሰራር ሊያይልን ይገባል ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ በሰጠው መግለጫ እንዳለው በሃጂ ተጓዦች ላይ የበረራ መስተጓጎል መፈጠሩን አምኖ፤ ለችግሩ መፈጠር የሃጂ አስተባባሪ ኮሚቴዎች ተጨማሪ ተጓዥ በመላካቸውና በሶማሊያ ክልል በተፈጠረው የጸጥታ ሁኔታ ምክንያት ከጅጅጋ የሚመጡ ተጉዋዦች በመዘግየታቸው መሆኑን አስታውቋል። መንገዳቸው ለተስተጓጎለባቸው መንገደኞችም የምግብና የማረፊያ ቦታ ማዘጋጀቱን ጠቅሷል።
የሃጂ ተጉዦች ግን አየር መንገዱ የሰጠውን ማስተባበያ እንደማይቀበሉትና ይህን ዓይነት ድርጊት ሆን ተብሎ በየዓመቱ እንደሚደረግ ገልጸው፤ ለደረሰባቸው የጊዜና የሞራል ኪሳራ አስተባባሪ ኮሚቴውና አየር መንገዱ ከተጠያቂነት አይድኑም ብለዋል።
በተያያዥ ምሽት ላይ በጣለው ከፍተኛ ዝናብ በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የትራፊክ መቆጣጠሪያ ክፍል ውስጥ ጎርፍ መግባቱን ተከትሎ የበረራ መዘግየት ተፈጥሯል።