የዓባይ ግድብን እየሠራ የነበረው ሳሊኒ የኮንስትራክሽን ኩባንያ መንግስትን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ካሳ መጠየቁ ተሰማ።

የዓባይ ግድብን እየሠራ የነበረው ሳሊኒ የኮንስትራክሽን ኩባንያ መንግስትን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ካሳ መጠየቁ ተሰማ።
( ኢሳት ዜና ነሐሴ 08 ቀን 2010 ዓ/ም ) የዓባይ ግድብን የሜካኒካል ስራ ኃላፊነት የወሰደው የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን በምህጻረ ቃሉ ሜቴክ፣ በኮንትራት የወሰደውን ሥራ በተቀመጠለት ጊዜ እና በትክክል ሰርቶ ማስረከብ ባለመቻሉ የጣሊያኑ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ሌሎች ስራዎችን መቀጠል አልቻለም ሲሉ ምንጮች ጠቁመዋል።
በዚህም ምክንያት ውሉ ያልተጠበቀለት ሳሊኒ ኩባንያ የኢትዮጵያን መንግስት ከ350 ሚለየን ዩሮ በላይ ካሳ እንደጠየቀ ለፕሮጀክቱ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ገልጸዋል።በወቅቱ ምንዛሬ መሰረት ሳሊኒ ኮንስትራክሽን የጠየቀው የካሳ ክፍያ፣ 10 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ይሆናል።
አጠቃላይ ግድቡ 84 ቢሊየን ብር ይፈጃል የተባለ መሆኑ ሲታወስ፣ አሁን ሳሊኒ የጠየቀው ካሳ ከአጠቃላይ የግድቡ ወጭ 8 ነጥብ 8 በመቶ ይሸፍናል። ምንጮቹ እንዳሉት፣ ግድቡ በጠቅላላው ስራ ይጀምራል በተባለበት ጊዜ ሜቴክ ኃላፊነቱን በወሰደው የሜካኒካል ስራው ችግር ምክንያት አስራ ስድስቱም ተርባይኖች መስራት አለመቻላቸው መንግስትን ጭምር እጅግ ያስደነገጠ ሆኗል።

የግድቡ ዋና መሃንዲስ የነበሩት ኢንጂነር ስመኜው በቀለ በቅርቡ በመኪናቸው ውስጥ ሞተው መገኘታቸው ይታወቃል። ፖሊስ ምርመራውን ውጤታማ በሆነ መንገድ እየቀጠለ እንደሆነና ውጤቱን በቶሎ ለሕዝብ እንደሚያሳውቅ ቢገልጽም፣ እስካሁን ድረስ ባለመነገሩ፣ ሕዝቡ በፖሊስ ላይ ግፊት እያደረገ ይገኛል።