“ሆላንድ ካር” በኪሳራ ምክንያት ተዘጋ

ህዳር ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- ከፍተኛ የመገናኛ ሽፋን አግኝቶ የነበረው በኢትዮጵያዊ እና በሆላንዳዊ በለሀብቶች የተቋቋመው የሆላንድ መኪና መገጣጠሚያ በኪሳራ ምክንያት መዘጋቱ ታውቋል። ኢትዮጵያዊው ኢንጂነር ታደሰ ተሰማ ከአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የውጭ ምንዛሬ በተለይም የዶላር የምንዛሬ ዋጋ መዋዠቅ እና ታክስ ከፍተኛ ችግር ፈጥሮባቸው እንደነበር መግለጻቸው ይታወሳል።

ጅጅጋ  ነው የተወለዱት።የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚያው ካጠናቀቁ በሁዋላ  የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጀነራል ዊንጌት ተከታትለዋል።በቀድሞው ሥርዓት  ከቀይ ሽብር ጥቃት በመሸሽ አገራቸውን ለቅቀው ተሰደዱ። ከዚያም አንድ ዓመት ተኩል በባህር ላይ ሢሰሩ ቆይተው ሆላንድ አገር ገቡ።የመኖሪያ ፈቃድ አገኙ። የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን ለስምንት ዓመታት በመከታተል አጠናቀቁ።

ኢንጂነር ታደሰ  ወደ ሥራ ዓለም ተሰማርተው ለ15 ዓመታት በሆላንድ ሢሰሩ በርካታ አሮጌ ላዳ መኪናዎችን ወደ አገር ቤት ይልኩ ነበር። ያን ያዩ ጓደኞቻቸው፦<<እንዴት እነዚህን አሮጌ መኪኖች ትልካለህ?”የሚል ጥያቄ ሲያከታትሉባቸው፤ ነገሩን አጤኑትና ስሜታቸው ተነካ።  “ወደ አገሬ አሮጌ መኪና ከምልክ፤ለምን  አዳዲስ የመኪና  ዕቃዎችን በመግዛት አገሬ ላይ አዲስ መኪኖች እንዲገጣጠሙ አላደርግም?” በሚል ሀሳብም፤ ያካበቱትን ዕውቀትና የቋጠሩትን ጥሪት በመያዝ ፤በሀሳቡ ካሳመኗቸው ሆላንዳውያን ጋር በመሆን አገራቸውንና ህዝባቸውን ለማገልገል  ወደ ኢትዮጵያ ተጓዙ። ሆላንድ ካር ኩባንያንም አቋቋሙ።በኢትዮጵያ  የመኪና መገጣጠሚያ ኩባንያ መቋቋሙን የሰሙ ሁሉ፤ ተስፋ አደረጉ።

ይሁንና በኢትዮጵያ ያለው የኢንቨስትመንትና የገበያ ድባብ ለሆላንድ ካር የተመቼ አልሆነም።

ላለፉት ኣመታት  አዋሽ፣እማይ፣ናዖሚ፣ተከዜ፣አባይ፣ሸበሌ የተባሉ አውቶቡሶችን በመገጣጠም ሲያመርት የቆየው “ሆላንድ ካር ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ” በደረሰበት ኪሳራ ምክንያት ሥራ ማቆሙን ዛሬ ራዲዮ ፋና ዘግቧል።

የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ ተሰማ  ሆላንድ ካር በኢትዮጵያ ቆይታው በዓመት 18 ሚሊዮን ብር ሢከስር ቆይቷል ብለዋል።

ኩባንያው ያጋጠመውን የገንዘብ እጥረት ለመፍታት ባለፉት አምስት ወራት ያደረገው ጥረት አለመሳካቱን የጠቀሱት አቶ ታደሰ፤ በአገሪቱ የሚታየውን የትራንስፓርት ችግር ለመቅረፍ ከሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት ጋር ተባብረው ሲንቀሳቀሱ ቢቆዩም፤ ላለፉት ሁለት ዓመታት ገበያ ባለመኖሩና ያለ ሥራ በመቀመጣቸው ለኪሳራ መዳረጋቸውን አብራርተዋል።

በመሆኑም ድርጅቱ በኢትዮጵያ የንግድ ህግ መሠረት በኪሣራ እንዲዘጋ ለፍርድ ቤት ማመልከቻ መፃፉን የዜናው ምንጮች ተናግረዋል።

በኩባንያው ውስጥ ሢሰሩ የቆዩ ሠራተኞችም ጥቅማ ጥቅሞቻቸው እንደሚከበሩላቸው ሥራ አስኪያጁ መናገራቸውን ምንጮቹ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በመኪና መገጣጠም ኢንቨስትመንት ዘርፍ የተሠማሩ እንደ መስፍን ኢንጂነሪን ያሉ የህወሀት ኩባንያዎች በመንግስት ጭምር ልዩ ልዩ ድጋፎች እንደሚደረግላቸው የገለጹት ምንጮች፤ በሞኖፖልና በአድሎ ከሚካሄደው ንግድና ኢንቨስትመንት  አኳያ- <ሆላንድ ካር> ከጨዋታ ውጪ መሆኑ አይገርምም ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ገንዘብ የከፈሉ 120 ያክል ደንበኞች መኪኖቻቸውን እንዲያገኙ ጥረቶች እየተደረጉ ነው ያሉት ኢንጂነር ታደሰ ፥ ጉዳዩ እንደተሳካ እናሳውቃለን ብለዋል።

___________________________________________________________________________________________________________________________________________________

ESAT is the first independent Ethiopian satellite service tasked to produce accurate and balanced news and information, as well as other entertainment, sports and cultural programming created for and by Ethiopians.

ESAT is committed to the highest standards of broadcast journalism and programming and will strive to provide an outlet of expression to all segments of the diverse Ethiopian community worldwide